ራሺያ ለአሜራካን እርምጃ የአጸፋ እርምጃ እሰጣለሁ አለች-በኮሪያ ጉዳይም አስጠነቀቀች

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የወሰኑት የራሺያ ኮንሶላር ይዘጋ ውሳኔ ዛሬ በሚተገበርበት ቀን የራሺያው የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሰርጊዪ ላቫሮቮ ሞስኮ ለዋሽንግተን እርምጃ የአጸፋ እርምጃዋን በቅርቡ ታሳውቃለች ያሉ ሲሆን ፕሬዚዳንት ፑቲን ደግሞ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ የአሜሪካ አቻቸውን አስጠንቀቀዋል።

ባለፈው ጥር ወር ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኦባማ አስተዳደር ጨፍግጎ የነበረውን የዋሽንግተንን እና የሞስኮን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ የምረጡኝ ዘመቻቸው ቃል ያሻሽላሉ ሲሉ ብዙዎች ተስፋ አድርገው ነበር።
በእርግጥ ፕሬዚዳንቱም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላቸው ደጋግመው የገለጹ ቢሆንም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በባሰ ደረጃ እጅግ የቀዘቀዘና በመጠቃቃት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረጋቸውን ተንታኞች ይናጋራሉ።

ከሁለት ቀናት በፊት በፕሬዚዳት ትራምፕ ቀጥተኛ ትእዛዝ እና ውሳኔ ራሺያ በሳንፍራንሲስኮ ያለውን ኮንስላራን እና በተጨማሪም በዋሽንግተን እና በኒዩርክ ያለውን የዲፕሎማቲክ ጽ/ቤቶቻን በሶስት ቀናት ውስጥ እንድትዘጋ ያሳወቁ ሲሆን እርምጃውንም ለሞስኮ ከ700በላይ የአሜሪካን ዲፕሎማት ቅነሳ ውሳኔ የአጸፋ መልስ ነው [tit-for-tat retaliatory measures] ሲሉ ተናግረዋል።

የአቦማ አስተዳደር የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ላይ ራሺያ በአሜሪካን ምርጫ ጣልቃ በመግባት ወ/ሮ ሂላሪ ክሊንተንን በትራምፕ እንዲሸነፉ አድርጋለች በሚል ውንጀላ 35 የራሺያ ዲፕሎማቶችን በማባረር እና የተወሰነ የዲፕሎማቲክ ንብረት የሆኑ ህንጻዎችን በመቆጣጠር እርምጃ ወስዶ የነበረ ሲሆን ራሺያም ከወራት ቆይታ በሃላ ከዋሽንግተን መሻሻል ሳይሆን መባባስን ስታይ በሀገራ ያሉትን የአሜሪካን ዲፕሎማቶችን ቁጥር በመቀነስና አንዳንድ የዲፕሎማሲ መጋዘኖችን በመዝጋት እርምጃ ወስዳ እንደነበር አይዘነጋም።

አሜሪካም ለዚህ እርምጃ የአጸፋ እርምጃ ያስፈልጋል በሚል ፕሬዚዳንታ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን ሞስኮም መውሰድ ያለብኝን እርምጃ አጥንቼ በቅርቡ የአጸፋ እርምጃዪን አሳታውቃለሁ ስትል በውጭ ጉዳይ ምኒስትራ በኩል አስታውቃለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የራሺያው ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ፑቲን በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አሜሪካንን በስመ ኒውክሌር መሳሪያ ቁጥጥር ከመጠን ያለፈ እርምጃና አካሄድ ዋሽንግተን ማድረጋን ኮንነው እንድትቆጠብ ያስጠነቀቁ ሲሆን አክለውም ሲናገሩ “ይህ በሁለቱ መካከል እየተካሄደ ያለው መዛዛት ወደ ሁለንተናዊ ጦርነት የሚያደርስ በመሆኑ መቆም አለበት ” ብለዋል።

ሐሙስና ዓርብ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ዓየር ሃይሎች በሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅራቢያ ሲለማመዱ መዋላቸውን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን በጃፓን በኩልም የአሜሪካን እና የጃፓን ወታደሮች ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዲጠጉ መደረጉን ዘግባል።

የራሺያና አሜሪካ ግንኙነት ከእግዜ ወደ ግዜ ከመሻሻል ይልቅ የመካረርና የመቆራቆስ አዝማሚያን የያዘ በመምጣቱ ሁለቱ ተፎካካሪ ሀገራት ወደ አልተጠበቀ ግንጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።