በተመልካች ድርቅ የተመታው ኢቢሲ የትርጉም ፊልም ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ETV/EBC አዋላጆቹ የሚል የኮርያ ፊልም አስተርጉሞ እንደጨረሰና እንደተዘጋጀ ተገለፀ፡፡ ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን የፊልም እንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን ባህልን ሊጎዳ እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደሳለኝ ሐይሉ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በሚተዳደረው ብሄራዊ ቴሌቪዥን የሌላን አገር ባህልና ምርት አምጥቶ ማራገፍ በራሱ የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነው በማለት ትችታቸውን ገልጸዋል። ይሄም  የባህል እና የኢኮኖሚ ወረራ እንደሆነም አክለዋል። የአገር ፍቅር ነጭ በመልበስ ሳይሆን ለአገር እና ለወገን የሚጠቅም ትውልድን በማፍራት ሊገለጽ እንደሚገባውም አብራርተዋል ፡፡

ደራሲ ቢኒያም ወርቁ በበኩሉ እደሜ ጠገቡ የድሮው ኢቲቪ የአሁኑ ኢቢሲ የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ንብረት መሆኑን አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የረሱት ይመስለኛል በማለት የራሱን ትዝብት አስፍሯል። ሲቀጥልም ይሄንን ትልቅ ድርጅት ለማስተዳደር አቅም፣ ችሎታና ብቃት እንደሌላቸው ነው እኔ የገባኝ በማለት ቅሬታውን አሰምቶአል።

በኣዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ወርቁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደራስያንን አወዳድሮ በመሸለም የተሻለ ስራ ይዘው እንዲቀርቡ ቢያደርግ የተሻለ ነበር ብለዋል።