ከሀገራችን የደቡብ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቀን ስራ እና መሰል ስራዎች ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ ወገኖች እየታፈሱ መሆናቸዉ ታወቀ

0

ረሃብ ከተከሰተባቸው ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ረሀቡን በመሸሽ ወደ ክልል ከተሞች በተለይም ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፉ ህፃናትና ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። ይህ ፍልሰት ደግም አገዛዛዙ  እያደረግሁ ነው ለሚለው የገፅታ ግንባታ አስጊ ሁኖ ስላገኘው ረሀብ ለመሸሽ የመጡትን ህፃናትና ወጣቶች እያፈሰ ወደአልታወቀ ቦታ እየወሰዳቸዉ መሆኑን ለትንሳኤ ሬድዮ የደረሰዉ መረጃ አመልክቷል።

ከአዲስ አበባ ካለፈዉ ቅዳሜ ነሀሴ 20 ቀን ጀምሮ ፖሊሶች ወጣቶቹን ከሚሰሩበት ጎዳናዎች ላይ እያፈሱና በአዉቶቡሶች እየጫኑ በመዉሰድ ላይ እንደሚገኙ የአይን እማኞች ሲገልፁ ወዴት እንደሚወስዷቸዉ ለጠየቁ ግለሰቦች “ወደሀገራቸዉ  እንድንመልሳቸዉ ታዘን ነዉ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸዉ ተናግረዋል። እማኞቹ እንደሚሉት በተለይ በአዲስ አበባ ዉስጥ ወጣቶቹ አዘዉትረዉ ለስራ በሚሰማሩባቸዉ አካባቢዎች ፖሊሶች እየተመላለሱ ሁኔታዉን ሲቃኙ እንደከረሙ እና አፈሳዉን በጀመሩበት እለት ማለዳ አዉቶቡሶቹ በየቦታዉ ቆመዉ መመልከታቸዉን አስታዉሰዉ አመሻሹ ላይ ሁሉም አዉቶቡሶች በወጣቶቹ ተሞልተዉ ጉዞ መጀመራቸዉን አስታዉቀዋል።

ከወጣቶቹ መሀል ከአምስት ጓደኞቹ ጋር አምልጦ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ አንድ ታዳጊ ለዝግጅት ክፍላችን እንደሚከተለው አስረድቷል። ፖሊሶቹ ሲወስዷቸዉ አካባቢውን እያቆሸሻችዉ ስለሆነ ወደአገራችሁ ትመለሳላችሁ በማለት እቃዎቻቸዉን ነጥቀዉ እና  አስገድደዉ ወደ አዉቶቡሶቹ ከአስገቡን በኋላ ወደ አዋሳ ወስደው  አዋሳ ዉስጥ በሚገኝ እና በቆርቆሮ በታጠረ  ሰፊ ሜዳ ዉስጥ ዘረገፉን። ታዳጊዉ ቅዳሜ እለት ከአዲስ አበባ የተነሳዉ አዉቶቡስ ቁጥር 31 መሆኑን እና አንዱ አዉቶቡስ መጫን የሚችለው  72 ሰዎችን ብቻ ሲሆን  በአንድ አዉቶቡስ ዉስጥ የነበሩት ወጣቶች ቁጥር ግን ወደ 90 የሚጠጋ እንደነበር  ገልጿል። አክሎም እሱ የተጫነበትን አዉቶቡስ ጨምሮ 9 የሚሆኑት ወደ አዋሳ ይወሰዱ እንጂ ሌሎቹ ወደየት እንደተወሰዱ አለማወቁን እና ታዳጊዉ አምልጦ ከመመለሱ በፊት ለሶስት ቀናት ያህል በተከለለዉ ሜዳ ዉስጥ  መቆየቱን ተናግሯል፡፡ የሚመገቡት ዳቦ እንደ እንሰሳ እየተወረወረ እንደሚሰጣቸዉ፣ በቂ የመጠጥ ዉሀም እንደማያገኙ እንዲሁም የሚያድሩት እና የሚፀዳዱትም እዛዉ ሜዳዉ ዉስጥ እንደሆነም ገልጿል።

ወጣቶቹም ታፍሰዉ የተወሰዱት ከሚሰሩበት ቦታዎች ስለነበር ለመኝታ የሚለብሱትም ሆነ ቅያሪ አልባሳት ያልያዙ ሲሆን ከመሀከላቸዉ ቁጥራቸዉ አነስተኛ ቢሆንም ሴቶችም እንደሚገኙበት እና ከወጣቶቹ መሀከልም ወደ ሀገራችን ወይም ወደ አዲስ አበባ መልሱን እያሉ ቢጠይቁም  ምላሽ እንዳልተሰጣቸዉ ታዉቋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሌላ በሌሎች ክልል ከተሞች ዉስጥም ፖሊሶች በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይ ከደቡብ የመጡ ወጣቶችን ከየመንገዱ እየያዙ ወደ ማሰልጠኛ ካንፖች እንደሚያስገቡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ምንጮች ይገልፃሉ። ከሶስት ሳምንታት በፊት በአማራ ክልል በሚገኘዉ ብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ዉስጥ ከሁለት መቶ ሀምሳ በላይ የሚገመቱ እና አማርኛ ቋንቋ ለመረዳት የሚቸግራቸዉ ወጣቶች እንደገቡም የዉስጥ ምንጮች ለትንሳኤ ሬድዮ ገልፀዋል። ምንጮቻችን እንደሚሉት የህወሓት አገዛዝ እየገጠመዉ ላለዉ የመከላከያ እና የሰራዊት እጥረት እነዚ ታዳጊ ህፃናት እና ወጣቶች በመጠኑም ቢሆን ሊቀርፉለት የሚችሉ መስሎት እየሰበሰባቸዉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ጥቂት የማይባሉት ከማሰልጠኛ ካንፖች እና ተጭነዉ ከሚመጡበት መኪናዎች ላይም እያመለጡ ወደመጡበት እንደሚመለሱም ምንጮቻችን ጨምረው ገልጸዋል። በአዲስ አበባ እየተደረገ ያለዉ አፈሳም እንደቀጠለ ሲሆን እስካሁን ያልተያዙት በስጋት በየቤቶቻቸዉ ተሸሽገዉ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡