በሁለተኛው የአለም ጦርነት በጀርመን ፍራንክፈርት የተጣለ ቦንብን ለማክሸፍ ከ60, 000 በላይ ሰዎች ከከተማው እንዲሸሹ ፖሊስ ማስገደዱ ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በሁለተኛው የአለም ጦርነት በእንግሊዝ ተጥሎ ሳይፈነዳ የቀረ ቦምብን ለማክሸፍ 65,000 የሚጠጉ ነዋሪዎችን የማሸሽ ስራ መጀመሩን ፖሊስ አስታወቀ።

ይህ1.4 ቶን የሚመዝነው የብርቲሽ ስሪት የሆነው ቦምብ የተገኘው አዲስ የህጻናት መዋያ ለመገንባት በሚደረግ የግንባታ እንቅስቃሴ እንደሆነም ታውቋል።

HS 4000 የሚባል መጠሪያ የያዘውን ቦንብ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ለማክሸፍ እንዲቻል በፍራንክፈርት ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎችና የአረጋውያን መቆያ እንዲዘጉ ተደርጓል።

ከ500 በላይ ታካሚዎችና አረጋውያንን ከሆስፒታሎች የማሸሽ ስራም እየተከናወነ እንደሆነም ተነግሯል።

አገሪቷ ካላት ጠቅላላ የወርቅ ሃብት ግማሹ ተከማችቶበታል የሚባለው ሴንትራል ባንክም ይህን የቦምብ ማክሸፍ ሂደት ተከትሎ እንዲዘጋ መወሰኑንም የዜና አውታሮች ዘግበዋል።

በጥንቃቄ ጉድለት ይህ ቦንብ ከፈነዳ ከፍተኛ ስፋት ያለውን የከተማዋን ክፍል ለማውደም እንደሚችል ፖሊስ ገልጻል።

በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀርመን ላይ ከተጣለው ቦምቦች ውስጥ በግምት እስከ 2000 ቶን ክብደት ያላቸው ያልፈነዱ ቦምቦችን በየአመቱ የማክሸፍ ስራ እንደሚደረግ ሪፓርቶች ያመለክታሉ።

በጀርመን የሚገኙ የቦምብ አክሻፊ ቴክኒሻኖች በትንሹ በየሁለት ሳምንት ውስጥ በአገሪቷ ሳይፈነዱ የቀሩትን ቦንቦችን የማክሸፍ አድካሚ ስራ እንደሚያከናውኑም ተገልጿል።

ይህ የማክሸፍ ስራም ምንአልባትም እስከ ሚቀጥለው አስር አመታት ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል ፍርሃት አለ።

በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጥቅም ላይ ከዋሉት 277 ሚሊዮን ቶን ቦምቦች ግማሹ በጀርመን ላይ የዘነበ እንደሆነም ተዘግቧል።

በጀርመን ዋና ከተማና የመንግስት መቀመጫ በሆነችው በርሊን ብቻ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የተጣሉ እስከ 400 ቦንቦች ተቀብረው እንደሚገኙ ይነገራል።

ከነዚህም ውስጥ ለማክሸፍ የተቻለው ወደ 200 ያህል ቢደርሱም ሙሉ በሙሉ ከተማዋን ከቦንብ አደጋ ነጻ ለማድረግ እንዳልተቻለ ተጠቅሷል።