የጸረ-ሙስናው ኮሚሽን 60 ሰዎችን አሰሬያለሁ አለ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በጠ/ይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ የሚመራው የኢትዮጵያ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በከፈትኩት ዘመቻ እስካሁን 60 ተጠርጣሪዎችን አስሬያለሁ ማለቱን የቻይናው የዜና ወኪል ሲን-ሃ ከአዲስ አበባ ዘገበ፡፡

ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት የተያዙት አምስት ተጠርጣሪዎች ቁጥር በእስከአሁኑ ጸረ-ሙስና ዘመቻ የታሰሩትን ሰዎች ጠቅላላ 60 እንዳደረሰው ለማወቅ ተችሏል።

ከ2015ቱ የኦሮሚያ አመጽ ጀምሮ በዓመቱ በተነሳው የአማራው ግዛት ሕዝባዊ ዓመጽ ምክንያት አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በመብት ጠያቂ ሰፊው ሕዝብ ተቃውሞ በመናጧ መንግስት አለብኝ ብሎ ካመነው የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግርን ለመፍታት ጥልቅ ተሀድሶ መውሰዱን በመግለጽ የጸረ ሙስና ዘመቻ እንደጀመረ መግለጹ ይታወሳል።

ሆኖም ዘመቻው የተነሳበትን ህዝባዊ ጥያቄና ሕዝባዊ ዓመጽ አቅጣጫ ለማስለወጥ የታለመ እንጂ መሰረታዊውን የሙስና ችግር ለመፍታት ታስቦ አይደለም ሲሉ የሰብዓዊ መብት ሞጋቾችና ፖለቲከኞች ያጣጣሉት ሲሆን የታየዙትም ሆነ የሚያዙትም የሙስናው ዋና ተዋናዮች ሳይሆኑ ጥቃቅኖች ናቸው ይላሉ።

እንደየቻይናው ዜና ምንጭ ዘገባ ከተያዙት አምስቱ ተጠርጣሪዎች መካከል ኢንጂነር አለሙ አምባዬ የንግድ መርከብ ድርጅት ም/ል ስራ አስኪያጅ፣ አቶ ሳሙኤል መላኩ የድርጅቱ ፋይናንስ ሃላፊ እንዳሉበት ገልጿል።