በናይሮቢው ሞይ ት/ቤት ስምንት ተማሪዎች ሞቱ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ስም በተሰየመው የናይሮቢው ሞይ አዳሪ ት/ቤት ዓርብ ለሊት በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የስምንት ታዳጊ ተማሪዎች ህይወት መጥፋቱን እና ከደርዘን በላይ የሆኑት ደግሞ በጸና መቁሰላቸውን የናይሮቢ ፓሊስ አስታወቀ።

በእሳት አደጋው ከተጎዱትና በጠና ከቆሰሉት ውስጥ የሁለት ተማሪዎች ቃጠሎ 60% የሰውነታቸው ክፍል መቃጠሉን ፖሊስ ገልጾ ህይወታቸውን ለማዳን የህክምና ባለሙያዎች እየተረባረቡ ነው ብሏል። የናይሮቢው ሞይ አዳሪ ት/ቤት የሴቶች ብቻ የሆነ በመሆኑ በእሳት አደጋውም የሞቱትና የተጎዱት ሁሉ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የኬኒያ ቀይመስቀል ድርጅት በበኩሉ ከሞቱትና ከተጎዱት በስተቀር የ10 ተማሪዎችን ስም ዝርዝር የጠፉ ብሎ ማውጣቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ዓርብ ወደ ቅዳሜ አጥቢያ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለእሳት አደጋ ሰራተኞች ችግር እንደፈጠረና ተማሪዎቹም በውጭ በኩል በሚቆለፍ ቁልፍ መኝታ ክፍላቸው የሚዘጋ በመሆኑ የተጎጂዎችን ቁጥር እንዳሳደገ ተገምቷል።

የናይሮቢ ፖሊስ የእሳቱን መንስኤ ለማጣራት ስራ ላይ መሆኑን ገልጾ ት/ቤቱም ለመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት መዝጋቱን አስታውቋል።

በኬኒያ አዳሪ ት/ቤቶች በእሳት መጠቃት ተደጋግሞ የተከሰተ ሲሆን ላለፉት ዓስር ዓመት ከሁለት መቶ በላይ ታዳጊ ተማሪዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይታወቃል።