በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መስሪያ ቤት ውስጥ ያለው ዘር ተኮር ተጽእኖ ዋና ስራ አስኪያጁን ስራ አስለቀቀ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

አቶ ኤርሚያስ እሸቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስኪያጅ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ባለው ዘር ተኮር ተጽእኖ የተነሳ ሃላፊነታቸውን መወጣት ስላቃታቸው ከሃላፊነታቸው እራሳቸውን ለማሰናበት እንደተገደዱ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል።

የአቶ ኤርሚያስን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መስሪያ ቤት እንዳይሰሩ ያገዳቸው ዘር ተኮር ችግር ዋና ስራ አስኪያጁ የመስሪያ ቤቱን አሰራር ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ ለማስተካከልና ለማዋቀር በቀረጹት አዲሱ ፕላን መሰረት ጥቅማችን ይነካብናል ብለው ያመኑ ያለብቃትና ችሎታ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ካድሬ መሰል እና ከገዢው የህወሃት ድርጅት ጋር ንክኪነት ያላቸው ሰራተኞች አልነካ ባይነትና ብሎም የመስሪያ ቤቱን ማስተካከያ መፈጸም አለመቻል እንደሆነ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በ2015 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መስሪያ ቤት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴውን እና ተግባራቱን በትግራይ በተገነቡ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ተደርጎ የተቋቋመ መስሪያ ቤት እንደሆነ የገለጹልን ምንጮቻችን አዲሱ የአቶ ኤርሚያስ እሸቱ መስሪያ ቤቱን ስራ ለማቀላጠፍና ሁሉንም በሚያገልግል መልኩ ለማድረግና የአጠቃላይ አገልግሎቱን ሁኔታ ለማሻሻል በሚል በአዲስ መልክ የማዋቀርን ስራን በሃላፊነት የመሩት ዋና ስራ አስኪያጅ ፕላናቸው ተፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን መንግስት የተቀበለው ቢሆንም በእሳቸው አመራር ስር እንዳይሆን የሚፈልጉት ሃላፊነታቸውና ችሎታቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች ለሰውዬው ስራ መልቀቅ ምክንያት እንደሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በሙያ ችሎታቸውና ብቃታቸው ተመስጋኝና ተመራጭ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ለፖለቲካዊ ተጽእኖ እና ለዘር ተኮር አሰራር ምቹ አይደሉም ሲሉ ይገልጻቸዋል። ሆኖም አቶ ኤርሚያስ እሸቱም ሆነ መንግስት የስራቸውን መልቀቅ ምክንያት ያልገለጹ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።