በቱርክ መንግስት ለእስር ከተዳረጉት ሁለት ጀርመናውያን አንዱ በነጻ መለቀቁ ተገለጸ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በ2016 የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርድዋንን ከስልጣን ለማውረድ ሙከራ ተደርጎ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የቱርክና የጀርመን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል።

ባሳለፍነው አርብ ለምርጫ ቅስቀሳ በጀርመን ቴሌቪዥን በተደረገው የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክር መርሃ መንግስት አንጌላ መርክልና ተፎካካሪያቸው ማርቲን ሹልትስ ቱርክ በጀርመናዊ ዜጎች ላይ ሆን ብላ የምታደርገውን ህገ ወጥ እስር ኮንነዋል እርምጃም እንዲወሰድባት ጠቁመዋል።

በፕሬዝዳንት ኤርድዋን የምትመራው ቱርክን ወደ አውሮፓ ህብረት ሙሉ በሙሉ የማካተትና አባል የማድረግ ሂደት በአፋጣኝ እንዲቆምም መርሃ መንግስት አንጌላ መርክል በዚሁ በቴሌቭዥን በተደረገ የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ገልጸዋል።

የቱርክ መንግስት ባሳለፍነው ሃሙስ ሁለት የጀርመን ዜጎችን አንታልያ ተብሎ ከሚጠራ የቱርክ አየር መንገድ በቁጥጥር ስር በማዋል ለእስራት እንደዳረጓቸው መዘገቡ ይታወሳል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ጀርመናዊያን አንዱ ከእስር ነጻ መለቀቁን በዛሬው እለት የወጣው መረጃ ያመለክታል። ሁለተኛው ግለሰብ ግን ያለበት ቦታና ሁኔታ እንደማይታወቅ በቱርክ የሚገኙ የጀርመን ዲፕሎማቶች እየተናገሩ ይገኛሉ።

በ2016ቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ላይ ተሳትፎ አላችሁ በሚል ክስ ከአስር ሺህ በላይ ዜጎችን የፕሬዝዳንት ኤርዶዋን መንግስት ለእስር መዳረጉ ተዘግቧል።

ይህን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የቱርክ መንግስት ንክኪ አላቸው የሚላቸውን ወደ 55 የሚጠጉ ጀርመናዊያንን በቁጥጥር ስር በማዋል ለእስር መዳረጉ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳውቋል። በእስር ከሚገኙት ጀርመናዊያን መካከል ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች እንደሚገኙበትም ሪፓርቶች ያመለክታሉ።

በአሜሪካ ፔንስሊቪያ በስደት የሚኖሩት የቀድሞው ኢማም ፌቱላሂ ጉሌን ከዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርድዋን መክሰሳቸውም ይታወቃል።

ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ምእራባውያንና የአሜሪካ መንግስት ይህ መፈንቅለ መንግስት እንደሚደረግብኝ ያውቁ ነበር እንደውም ሲያስተባብሩ የነበሩትን ግለሰቦችንም ከለላ ሰጥተዋል በማለት ወቀሳቸውን ያሰማሉ።

ከመፈንቅሉ መንግስት ሙከራ በሃላ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን አገራቸው ከምእራባውያን ጋራ ያላትን የውጭ ግንኙነት በማላላት በፕሬዝዳንት ፑቲን ከምትመራው ሩሲያ ጋራ ጠንካራ የፓለቲካና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መፍጠራቸውም ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸው በሃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራውን የኢትዮጵያን መንግስትንም በኢማም ፌቱላሂ ጉሌን ስር የሚገኙትን ድርጅቶችና ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጋ መጠየቃቸውም ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ለአስር አመት በትምህርት ዘርፍ ተሰማርቶ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የአል ነጃሲ ኢትዮ ቱርክ ትምህርት ቤትንም ከፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ይፋዊ የኢትዮጵያ ጉብኝት በኋላ ከጉሌን ድርጅት እንዲወጣና እንዲሸጥ መደረጉ ይታወቃል።