በሎሬት ቴውድሮስ ካሳሁን ላይ የተላለፈው ውሳኔ ከህወሃት ኤልት ክፍል ነው ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ
በአርቲስት ሎሬት ቴውድሮስ ካሳሁን [ቴዲ አፍሮ]የእሁድ ነሀሴ 28ቀን 2009ዓ.ም የኢትዮጵያ አልበም ምርቃት ፓርቲ መሰረዝ ትእዛዝ የተሰጠው የገዢው ፓርቲ አስካል ከሆነው የህወሃት የላእላይ ኤሊት ክፍል መሆኑን ምንጮች የገለጹ ሲሆን በአንጻሩም ውሳኔው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ትችት ነቀፌታን በመፍጠር ለአርቲስቱ ታላቅ የሆነ አጋርነትን እና ዘመቻን በመክፈት እርምጃውን “የዳዊትና የጎሊያድ” ስያሜን እንደሰጡት ለማወቅ ተችላል።
በማህበራዊ ድረ ገረ-ገጾች፣በአዲስ አበባና በመላው ዓለም በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መንደር ውስጥ ኢትዮጵያዊያኑ የእውቁን አርቲስት ሎሬት ቴዲ አፍሮ ፓርቲ መሰረዝን በመቃወም ታላቅ የሆነ የአጸፋ መልስ ሲዥጎደጎድ ለማየት የተቻለ ሲሆን በዚህ የህዝቡ እርምጃና ውሳኔውን የሰጠውን አካል፣የሰጠበትን ምክንያት ዙሪያ የተጠናቀረውን ልዩ ዘገባ እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።

*** የሎሬት ቴዲ አፍሮና የህወሃት ሁኔታ-የዳዊትና የጎሊያድ ፍልሚያ ነው-

ለአንድ ሺህ ሰዎች የጥሪ ወረቀት ተበትናል።አርቲስቶችና የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች በሙሉ የተጋበዙ ሲሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣የታሪክ ምሁራን፣አትሌቶች፣ፖለቲከኞችና ተራ ሰዎች በዚህ የነጻ መግቢያ በተዘገጃለት የሂለተኑ የነሀሴ 28ቀን 2009ዓ.ም ኢትዮጵያ አልበም ምርቃት እንዲታደሙ በክብር ተጋብዘዋል። በልዩ የክብር እንግድነትም አጼ ቴውድሮስና የእውቁ ጸሃፊ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ ወራሽ ቤተሰቦችም እንዲገኙ ተጋብዘዋል።

አልበሙ ካካተታቸው 14ዘፈኖች ውስጥ “ጎጃም ጉራማይሌ” ቪዲዮ ክሊፕ ለአልበሙ ምርቃት ቀረጻው ተጠናቆ ተዘጋጅታል። ስነ-ግጥም፣መነባንብ በተለያዩ ከያኒያን ተዘጋጅቶ የመድረኩን ሰዓት ይጠባበቃል።

የሂለተን ሆቴል ግራውንድ ቦልሩም በልዩ ሁኔታ እራሱን አዘጋጅቶ እንግዶቹን በሚጠባበቅበት እሁድ እለት ከጣቱ አምስት ሰዓት ጀምሮ በመጀመሪያ በስልክ ጥሪ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተደውሎ የሎሬት ቴዲ አፍሮን ፓርቲ ማስተናገድ እንደሌለበት ይነገረዋል። ለሆቴሉ ማኔጅመንት በመጀመሪያ የተገለጸለት ምክንያት አልነበረም። በደፈናው ፓርቲውን ማካሄድ እንደማይገባው በመግለጽ የሚያስጠነቅቅ ትእዛዝ ብቻ ነበር።

እለቱ እሁድ ከመሆኑም ባሻገር አጠቃላይ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ከሐሙስ ጀምሮ ለተከታታይ 10ቀናት “የኢትዮጵያ ከፍታ”በሚል መርህ ሀገሪቷ በፓርቲ ላይ ያለች ሆና ሳለ የትኛው የመንግስት ባለስልጣን ነው በስራ ላይ ሆኖ ይህንን መሰረት የለሽ ትእዛዝ የሚሰጠው በሚል እምነትና ብሎም ሆቴሉ ለንግድ ስራ የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን ገንዘቡን ከፍሎ ለመስተናገድ ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ለከፈለበትም ሆነ ለሚከፍለው ገንዘብ አገልግሎት መስጠት ግዴታው መሆኑን በመግለጽ በፕሮግራሙ ይጸናና ዝግጅቱን ይቀጥላል።
በቀጣዮቹ ሰዓታቶች ውስጥ ከተለያየ አቅጣጫ የስልክ ጥሪ ሲዥጎደጎድበት የተደናገጠው የሂልተን ሆቴል ማኔጅመንት ጉዳዩን ለሚመለከተው አርቲስት ሎሬት ቴዲ አፍሮ ተወካዮች ሶስቱ ድርጅቶች በመደወል ያሳውቃል። ብሎም በማኔጅመንቱና በአዘጋጆቹ መካከል አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በህጋዊነቱ ዙሪያ ምክክር ከተደረገ በኋላ ፕሮግራማቸውን ለመሰረዝ የሚያበቃ አንዳችም ምክንያት በማጣት ዝግጅቱን ለማካሄድ ሲወስኑ አርቲስቱንም ጉዳዩን እንዲያውቅ ያደርጋሉ።

ከሰዓት በኋላ ከደህንነት ቢሮ ጌታቸው አሰፋ ጭምር ለሂልተን እንደተደወለና ቀጭን ትእዛዝ እንደተሰጠው ምንጮቻችን ይናገራሉ ሆኖም ሆቴሉ የተከፈለበትን የአልበም ምርቃት ድግስ ገንዘብ ተቀብሎ፣ለአንድ ሺህ ሰው ምግብ፣መጠጥና አዳራሽ አዘጋጅቶ የመጨረሻው ሰዓት ላይ ለአርቲስት ሎሬት ቴዲ አፍሮ አይቻልም የሚልበትን አንዳችም ምክንያትና ጥፋት ያጣበታል። ማኔጅመንቱ እገዳው ከህግ አንጻር ሳይሆን ከፖለቲካ አንጻርና ብሎም ከብቀላ አኳያ እንደሆነ በመረዳት በማገዱ ላይ እንደማይተባበር በድጋሚ በስልክ እየደወለ ትእዛዝ ሲሰጠው ለነበረው ሃይል በመግለጽ ፓርቲውን ለማስተናገድ መወሰኑን ይገልጻል።ይህንንም ውሳኔውን ለፓርቲው አዘጋጆችም ያሳውቃል።

በዚህ ግዜ የሀይል እርምጃን አስፈላጊነት ያመነው አጋጁ ስውር ሃይል የታጠቁ የአግዓዚ ሰራዊት አባላትን በፍጥነት በመላክ ዓለም አቀፉን ሂልተን ሆቴልን ያጥለቀልቃል። ወታደሮቹ የፌዴራልም ሆነ የአዲስ ፖሊስ እንዳልሆኑ ታይተዋል።ቱሪስቶች እና የውጭ ዜጎች ምን ተፈጠረ በሚል ትንግርትና ፍርሃት ጉዳዩን ሲከታተሉ ተስተውለዋል። ከወታደሮቹ ሆቴሉን መውረር በኋላና መጨረሻም ማገድ መቻላቸው ያለው ድራማ እራሱን የቻለ ዘገባ ያስፈልገዋል።
**የውሳኔው ምንጭና ምክንያት-

ውሳኔው መንግስታዊ ሳይሆን ድርጅታዊ ብሎም የህወሃት ፓርቲ ላእላይ ውሳኔ መሆኑን ምንጮቻችን ይናገራሉ።ያቀረቡትም አሳማኝ ምክንያት በርካታ ቢሆንም አንዱን ለመጥቀስ ያህል በእሁድ ምድርና በሀገር አቀፍ ደረጃ ስራ የለም ተብሎ ተብሎ ሁሉም እረፍት ላይ ባለበት ሰዓት ስልክ መደወልና ብሎም የአግዓዚን ሰራዊት ማዘዝ የሚችል ብቸኛው የሰራዊቱ አዛዥ ህወሃት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አርቲስት ሎሬት ቴዲ አፍሮ በህወሃት መራሹ መንግስት ከ1997ት ጀምሮ ጥርስ የተነከሰበት አርቲስት ቢሆንም በተለይ ከኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ውስጥ ህወሃት ደግሞ በተለይ ሁኔታ አርቲስቱን በድርጅታዊ ኔት ወርካቸው ውስጥና በካድሬዎች ዘንድ በስርዓቱ ጠላትነት ተፈርጆ በየእለቱ የሚገለጽ አርቲስት የሆነ ሲሆን በአዲሱ ኢትዮጵያ አልበም ያቀነቀነላቸው የአጼ ቴውድሮስ ዜማም የወቅቱ መበሳጫቸው ስራው እንደሆነ ተነግሯል።

በህወሃት ካድሬዎች ዘንድ ለምን ስለ አጼ ዮሃንስ ሳይዘፍን ስለ አጼ ቴውድሮስ ዘፈነ የሚል ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ መፍጠሩና ብሎም ኢትዮጵያ ብሎ ያዜመው እኛ የምንመራትን ኢትዮጵያ አይደለችም በማለት አርቲስቱን በሀገሩ ምድር ከሕዝብ ጋር ላለማገናኘት ቀደም ብሎ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ሆኖም እገዳው ይፋ በሆነ ደቂቃዎች ውስጥ በውሳኔው የተበሳጩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳዮን ወደ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመውሰድ አርቲስቱን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ያነገሱት[Glorify]ሲሆን ብዙዎችም ግብግቡን የዳዊትና የጎሊያድ ሲሉ ገልጸውታል።
የአባይ ሚዲያ ለአንባቢዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየታችሁን ግለጹልን ብሎ በፌስ ቡክ ገጹ ላቀረበው ጥያቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ልዩና ድንቅ በሆነ ሁኔታ ለአርቲስቱ ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ አስፍረዋል።

“ሎሬት ቴዲ አፍሮ ብቻህን መንግስትን ያጋለጥክና ዝርክርኩን ያወጣህ” ሲል አንድ አንባቢ አስተያየቱን ያሰፈረ ቢሆንም የአብዛኞቹ መልእክት ተመሳሳይ ከመሆኑ አንጻር ልንመርጠው ችለናል።