የኬኒያ ተቃዋሚዎች በሰጡት ቅድመ ሁኔታ በጥቅምት 17ቱ ምርጫ ለመሳትፍ ዘመቻ ጀመሩ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ሁለተኛውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጪው ጥቅምት 17ቀን 2017 እንዲካሄድ በወሰነ ማግስት ዛሬ ማክሰኞ ዋናው ጥምር የተቃዋሚዎች ህብረት [NASA]መሪ አቶ ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው ቦርድ መሪን ባላካተተው የምርጫ ቦርድ ድርጅታቸው እንደሚሳተፍ በመግለጽ የምረጡኝ ዘመቻ የጀመሩ ሲሆን ገዢው ፓርቲም [Jubilee ]በበኩሉ የሚካሄድ ለውጥ የለም ሲል መልሷል።

የኬኒያው ጠ/ይ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓርብ የነሀሴ 8ቀን 2017ቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ ካደረገ ውሳኔው በኋላ ትናንት ሰኞ በተካሄደው የምርጫ ቦርዱ [IEBC] የምርጫውን ቀን ይፋ ማድረግ ጀምሮ ባሉት ክስተቶች ላይ የተቀናበረው ልዩ ጥንክር እንደሚከተለው ቀርባል።
*** የኬኒያ ዴሞክራሲን መሰረት ያጠናከረው ውሳኔ-

የኬኒያው ጠ/ይ ፍርድ በአፍሪካ የመጀመሪያ ያደረገውን የዓርብ እለቱ ውሳኔ ሀገሪቷን እጅግ ውድ ለሆነው የምርጫ ሂደት ሁለተኛ ዙር በመጪው ጥቅምት 17ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ተክትሎ ከተቃዋሚው በኩል ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ እለት ጀምሮ ሲገልጽ የነበረውን የምርጫ ቦርዱ ይቀየርልን ጥያቄን በድጋሚ ይዞ እንዲቀርብ አድርጎታል።
`

አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ “አጭበርባሪ “ብለው የገለጹት የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ነጻ፣ገለልተኛ እና ፍትሃዊ የሆነ የምርጫ ሂደት ማከናወን አለመቻሉን በጠ/ይ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔን ዋቢ በማድረግ ድርጅቱ ዳግም ዳግም የምርጫ ሂደትን በበላይነት ሊመራ የሞራል ብቃት ይጎድለዋል ብለው የሚያምኑ ሲሆን እምነታቸው ግን በገዢው ፓርቲ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘላቸው አልሆነም።

ሆኖም ራይላ በምርጫ ቦርድ ኮሚሸነር መለወጥ ቅድመ ሁኔታን ቢያስቀምጡም ዛሬ ግን ለደጋፊዎቻቸው የምረጡኝን ዘመቻ የከፈቱ ሲሆን በፕሬዚዳንቱ ተከታትሎ የተሰነዘረውን ትችትና ነቀፌታን መልሰው በማጥቃት ደረጃ የፍርድ ቤቱን ዳኞች ተከላካይ ሆነው ውለዋል።

ከ20በላይ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትና አሜሪካ በየአምባሳደሮቻቸው በኩል ለጠ/ይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያላቸውን አድናቆትና ክብር የገለጹ ሲሆን የምርጫ ቦርድም ስህተቶቹን አርሞና አስተካክሎ እውነተኛ ምርጫ ማካሄድ ይቻለዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
በ2013ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክር ሁሩ ኬኒያታን አሸናፊ አድርጎ ያወጀው የጠ/ይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔን ፕሬዚዳንቱ አድናቂና አንቆለጳጳሽ ሆነው ሳለ ዘንድሮ በተመሳሳይ መልኩ ፍርድ ቤቱ አሸናፊነታቸውን ውድቅ በማድረጉ አጠቃላይ የፍርድ ቤቱን መዋቅር ሊተቹም ሆነ ሊያጠቁ አይገባም ሲሉ ኬኒያዊያን ለሰሞኑ የፕሬዚዳንት ሁሩ ኬኒያታ ጸረ-ፍርድ ቤት ንግግሮች መልስ ሲሰጡ ታይተዋል።
`
ፕሬዚዳንት ሁሩ ኬኒያታ በዓርቡ እለት የጠ/ይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔን ፍትሃዊ አይደለም ግን ተቀብዬዋለሁ ባሉ ማግስት ተከታታይ ቀናቶች ውስጥ ፕሬዚዳንቱ የተቆጩ ይመስል ጠንከርና ጠጠር ያለ ትችት፣ነቀፋና ውግዘትን ማዥጎድጎዳቸው በሁሉም አቅጣጫ የተነሳ ህዝባዊ ትችት እንዲነሳባቸው አድርጋል።

በመጪው ጥቅምት 17ቀን ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው ሃይል የጠ/ይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይጠቀምበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ኦዲንጋ ከወዲሁ ፕሬዚዳንቱን በ1.5ሚሊዮን ድምጽ ብልጫ ነው ያሸነፍኩት እያሉ እንዲገልጹ ያስቻላቸው ሲሆን ብዙዎችም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፕሬዚዳንቱ ድምጽ ሰርቀው አሸንፌያለሁ ብለው እንዳወጁ አድርገው እንዲያዩ አስችሏቸዋል።