ሰሜን ኮሪያ አህጉር ተሻጋሪ ሚሳይል [ICBM] ለመተኮስ ተዘጋጅታለች ተባለ-ውጥረቱም ተካሯል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ሰሜን ኮሪያ በሰዓታት ውስጥ ሌላ አህጉር ተሻጋሪ ባልስቲክ ሚሳይል [ICBM] ለመተኮስ በዝግጅት ላይ ነች ስትል ደቡብ ኮሪያ ማስታወቋን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።

የአሜሪካን ወታደራዊ ጠበብቶች በሰሜን ኮሪያ ላይ ሊወሰድ በሚችለው ወታደራዊ እርምጃ ላይ ቢመክሩም ክስምምነት ላይ የሚያደርስ ፕላን ማግኘት መቸገራቸውን ዘገባዎች እየገለጹ ሲሆን ራሺያና ቻይና በሌላ ወገን ማንኛውንም የሀይል እርምጃን በጥብቅ እያወገዙ ባለበት ሁኔታ ደቡብ ኮሪያ በተናጠል ወደ ወታደራዊ እርምጃ ለመግባት በመፈለግ እርምጃዎችን እየወሰደች እንዳለ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በኮሪያ ልሳነ ምድር በተነሳው ውዝግብ ዙሪያ የተጠናቀረው ወቅታዊ ዘገባ ቀጥሎ ቀርቧል።

***የሰሜን ኮሪያ ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ እና ለምእራባዊያን ስለላ ተቋማት መታወቅ ያልቻለው ተቃውሞቿ-

የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ግዜ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ላይ ማክሰኞ የመከረ ቢሆንም ያስተላለፈው ውሳኔ ግን ቀውሱን መፍታት የሚቻለው በዲፕሎማሲ ብቻ ነው በማለት የራሺያን እና የቻይናን አቋም አንጸባርቋል።

የፒዮንጊያንግ እሁድ እለት የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ሙከራ ማግስት የተካረረው ውጥረት ከኮሪያ ልሳነ ምድር ተሻግሮ በዋሽንግተን፣ኒዮርክ፣ብራሰልስ፣ሞስኮና ቤጂንግም በመዝለቅ መሪዎቹን መውሰድ በሚገባቸው እርምጃ ዙሪያ መወሰን እስኪያቅታቸው እንዲጨነቁ አድርጓል።

የእሁዱ የሰሜን ኮሪያ ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ከተለመደው ኒውክሌር በእጅጉ እንደሚልቅ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። የቦምቡን ሃይለኛነትና ቴክኖሎጂውን ሳይንቲስቶቹ ሲገልጹ በ1944 ሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሜሪካ በሂሮሺማ ከጣለችውና ከ80ሺህ በላይ ሰዎችን ከፈጀው የኒውክሌር ቦምብ ሃይል ጋር ሲነጻጸር ሃይድሮጂን ቦምብ በ1000% በልጦ ያለ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ይህ ሃያል የማጥፋት አቅምና ሃይል ያለውን ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ እሰከ ዛሬ ድረስ ከታወቁት አምስቱ ሀገራት [አሜሪካ፣ራሺያ፣ቻይና፣ፈረንሳይና እንግሊዝ]በስተቀር ሌሎች እነደ ህንድ፣ፓኪስታን አይነቶቹ ሀገራት ቴክኖሎጂውን ስላልደረሱበት እንዳሌላቸው የተገለጸ ሲሆን እሁድ በሰሜን ኮሪያ የተሞከረው ግን በተፈለገ ደረጃና መጠን በሚሳዪሎች ላይ ተገጥሞ ኢላማውን መምታት ይቻለዋል ሲሉ ይገልጻሉ።
የአሜሪካን፣ደቡብ ኮሪያም ሆነ የጃፓን ታላቅ ስጋት አሁን ፒዮንጊያንግ ቀደም ሲል በሞከረቻቸው አህጉር ተሻጋሪ ቦለስቲክ ሚሳዪሎቻ ተጠቅማ ይህን ሀገር አውዳሚ ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ በመጠቀም ታጠቃናለች በሚል እድምታ ቴክኖሎጂዋን ማውደም አለብን ባዮች ሆነዋል።

ሆኖም የሰሜን ኮሪያን ኒውክሌርና ሚሳዪሎችን ለማውደም ምእራባዊያን እንዲሁ በቀላሉ የሚቻላቸው አይደለም በማለት ወታደራዊ ጠበብቶች ሲያስረዱ የትኛውም የአሜሪካን ሰሜን ኮሪያ ማጥቃት እርምጃ መወሰድ በመጀመሪያ ደረጃ ሴኡልን[ደቡብ ኮሪያ]እና ጃፓንን መውደም ያስከትላል ባይ ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፔንታጎን የጦር ኤክስፐርቶች በቀረበላቸው የተለያዩ ወታደራዊ እርምጃዎች ላይ እንዳልተስማሙና መወሰንም እንደተቸገሩ ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን የሰሜን ኮሪያ መሳሪያዎችና ማምረቻ ተቋሞች ስፍራ መታወቅ አለመቻል ለፔንታጎንና ለዋይት ሃውስ ሌላኛው የራስ ምትታ ምንጭ መሆኑን ይገልጻሉ።

በምእራባዊያን ባህታዊው ስርዓት ተብሎ ስለሚገለጸው የፒዮንጊያንግ ገዢ ፓርቲ ምስጢራዊነት የስለላ ተቋማቱ የሳተላይት እርዳታን በመጠቀምም ሆነ የከዱ ሰሜን ኮሪያዊያንን በመጠቀም እስከዛሬ ድረስ ስለ ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ይዞታዎችና ስለጦር መሰሪያዎቿ በቂ መረጃ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ይነገራል።

በጸጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ “ኮም ጆንግ አን ለጦርነት እየተማጸነን ነው።ኑ ግጠሙኝ እያለ ጦርነት እየለመነን ነው” ብለው ለምክር ቤቱ ከገለጹ በኋላ አክለውም “አሜሪካ ግን በአሁን ወቅት ከፒዮንጊያንግ ጋር ለመዋጋት አትፈልግም። ሆኖም ትእግስታችንም ወሰን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ከአምስቱ የኒውክሌር አባል ሀገራት ጋር አቻ ያደረጋትን ቴክኖሎጂ ጨብጣለች የሚሉት ሌላው ወታደራዊ ተንታኝ አሜሪካም ህነች ሌሎች ምእራባዊያን ሃይሎች እጃቸውን ዘርግተው ፒዮንጊያንግን በአባልነት በመቀበል ያለባትን የህልውና ጥያቄን በሰላም ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ሲሉ ይገልጹና ሲያጠቃልሉም ዋሽንግተን ይህን አማራጭ ትታ በሃይል እርምጃ ሰሜን ኮሪያን ትጥቅ አስፈታለሁ የምትል ከሆነ ለምትከፍለውም እልቂት መዘጋጀት ይኖርባታል ሲሉ ይናገራሉ።

ሰውዪው[የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ አን ማለቴ ነው] በቀላሉ ከመደምሰስ ደረጃ መራቁን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዋሽንግተን እና አጋሮቿ መደምሰስ አለበት ብለው ጦርነት ቢከፍቱበትና መጨረሻም መደምሰስ ቢቻላቸው እንኳን ከደቡብ ኮሪያ፣ጃፓን ጀምሮ በከፊል አሜሪካንንም በማውደም ዋጋ ብቻ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ አንጻር ማየት ይቻላል። በሌላ አንጻር ደግሞ አሜሪካ የሰውዪውን የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ባለቤትነት አምኖ በመቀበል የማህበሩ አባል ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም [Over my dead body ] ዓይነት የሆነ እርምጃ ነው።

የሰላሳ አራት ዓመቱ ወጣቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ አን ሀገሩ እንደ አባቱና አያቱ ዘመን በማእቀብ ዳሽቃና ከዓለም ተገልላ የነበረችበትን ሁኔታ ሰብሮ በመውጣት አዲስ ዓለም ለመፍጠር የወሰነ ሆኗል።ቻይና እና ራሺያ ደግሞ የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሃይል እርምጃን የሚያጸድቅ ውሳኔን እንዳይሰጥ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብታቸው በመጠቀም መከላከላቸውን ገፍተውበታል።

የኮሪያ ልሳነ ምድር አዲስ ምእራፍ ላይ ይገኛል-በቅርቡም አዳች ሃያል የሆነ ሀይል ከአካባቢው ይነሳል ተብሎ ተገምቷል፡፣