ጋዜጠኛዋ በቤቷ ደጃፍ በጥይት ተመትታ መገደሏ ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በጋዜጠኝነት ሙያዋ ታታሪና ደፋር እንደሆነች የሚነገርላት የ55 አመቷ ጋዜኛ ላንኪሽ ደረቷ እና ጭንቅሏቷ ላይ በተተኮሰ ጥይት ህይወቷ ሊያልፍ እንደቻለ ተዘግቧል።

የተወሰኑ የቀኝ ክንፍ ደጋፊና አባላት  ጋዜጤኞችን የመግደል እቅድ እንዳላቸውና ከሚገደሉት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ሳትኖርበት እንደማትቀር ጋዜጠኛ ላንኪሽ  ለሙያ አጋሮቿ ቀደም ብላ ስትናገር እንደነበረም ተገልጿል።

ደፋርና አንደበተ ርእቱ መሆኗ የሚመሰከርላት ይህች ጋዜጠኛ በስልጣን ላይ ያሉትን ሚኒስትሮች ጨምሮ አክራሪ የሂንዱ ናሽናሊስትንም በመተቸት ትታወቃለች።

የዚህችን ጋዜጠኛ ህይወት አጥፍቷል ተብሎ በፓሊስ ፍለጋ ላይ ያለው ግለሰብ በሞተርሳይክል በመሆን ጋዜጠኛዋ ላይ ክትትል ሲደረግባት እንደነበረ የፓሊስ ሃላፊዎቹ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በሚመራው የህግ አውጪ ክፍል ውስጥ የሙስና ተግባር ተፈጽሟል በማለት ባሳለፍነው አመት ባወጣችው ጽሁፍ ይህች ጋዜጠኛ ለክስ ቀርባ የስድስት ወር እስራት ቅጣት ተበይኖባት በዋስ እንደተለቀቀች ይታወቃል።

በዲሞክራሲና በነጻነት በመናገር መብት እንደምታምንና ትችትንም የማትፈራ ጋዜጠኛ እንደሆነች ከዚህ በፊት ለሚዲያ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ተናግሯለች።

በምእህጻረ ቃል (BJP) በመባል የሚታወቀውን በስልጣን ላይ ያለውን የህንድ ገዢ ፓርቲን እንዲሁም የሚያራምደውን የሂንዱ ናሽናሊዝም ርእዮተ አለምን የሚተቹ ጋዜጠኞች በማህበራዊ ሚዲያ የማስፈራሪያ ቃላት እንደሚሰነዘርባቸው በተለይ ደግሞ እንስት ሪፓርተሮች የአስገድዶ መድፈር ዛቻ እንደሚደርስባቸው  አክቲቪስቶች ገልጸዋል።

የጋዜጠኛ ጋሪ ላንኪሽ ግድያ ያስቆጣቸው በርካታ ሰዎች በዋናዋ ከተማ ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ ከተሞች ንዴታቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ መውጣታቸውም ተዘግቧል።

በቲውተር ገጽም በጋዜጠኛዋ ህይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሃዘን በርካታ ሰዎች እየገለጹ ሲገኙ በተቃራኒው ግድያውን የሚደግፉም አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ።