የተቋዋሚ ፓርቲ መሪው በመኖሪያ ቤታቸው በተከፈተባቸው የተኩስ እሩምታ ክፉኛ ተጎዱ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በታንዛኒያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቱንዱ ሊሱ በመኖሪያ ቤታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰባቸው ጥይቶች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል እንደገቡ ተነገረ።

እኚህ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የፓርላማ አባል የሆኑት ቱንዱ በስልጣን ላይ ያለውን የታንዛኒያን መንግስትና ፕሬዝዳንቱን በተደጋጋሚ በግልጽ ሲተቹና ሲቃወሙ እንደነበረም ተገልጿል።

በደረሰባቸው ጉዳትም ለቀዶ ጥገና በዋናዋ ከተማ ወደ ሚገኘው ሆስፒታል በአፋጣኝ እንዲገቡ መደረጉንም ታውቋል።

ተቃዋሚው በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን አምባገነን በማለት በሰነዘሩት ትችትና ተቃውሞ በቅርቡ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

ቻዴማ በመባል የሚጠራውን የተቃዋሚ ፓርቲ በሚመሩት ቱንዱ ሊሱ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ መንስኤውን ወይም ምክንያቱን እያጣራ እንደሆነ  ፖሊስ ተናግሯል።

የቀዶ ጥገናው በተሳካ ሁኔታ እንደተደረገላቸውና የተተኮሱባቸው ጥይቶችም ከሆዳቸው ለማውጣት እንደተቻለም የህክምና ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ መረዳት ተችሏል።