ከባቢሌ እስከ ሞያሌ ግጭቶች ተባብሰዋል-በሞያሌ 12 ሰዎች ተገድለዋል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በኦሮሚያና ሱማሌ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የሚካሄደው ወታደራዊ ግጭት መባባሱ ከስፍራው የሚደርሱ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን በሞያሌ አቅራቢያ ብቻ ዛሬ 12 ሰዎች መገደላቸውን ቪ.ኦ.ኤ የዘገበ ሲሆን ጦርነቱ አሁንም እየተካሄደ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

የኦሮሚያ መስተዳድር የመገናኛ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ለቪ.ኦ.ኤ ራዲዮ በሰጡት ቃል በምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ ከሱማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ስፍራዎች ግጭቶች መኖራቸውን እና የህይወት መጥፋት መከሰቱንም አምነው የተናገሩ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ያጠናቀርነው ዘገባ ቀጥሎ ቀርቧል።

*** ከባቢሌ እስከሞያሌ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በሱማሌው ልዩ ፖሊስ ሃይል የተከፈተው ጥቃት-

የኢትዮጵያ እና ኬኒያ ድንበር ከተማና ባለ ሁለት ቀበሌ የሆነችው ሞያሌ ከተማ ያላትን ሁለት ቀበሌዎች ለክልል 4 [ኦሮሚያ]እና ክልል 5 [ሶማሌ]ዞን አካፍላ ያለች የሁለት ክልላዊ መስተዳድሮች ከተማ ስትሆን በከተማይቱ ውስጥ ብዙሃን በሚባሉት የኦሮሞ ቦረና ጎሳዎች እና አናሳ በሚባሉት የሶማሊ ገሪ ጎሳዎች መካከል ተደጋግሞ የተከሰተ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ያስተናገደች ከተማም ነች።

በጨሙቅና ጎፋ የሞያሌ ገጠራማ ቀበሌዎች በኦሮሚያ መስተዳድር ስር ያለ የቦረና ተወላጆች መንደር ቢሆንም ከሶማሌው ዞን 5 ልዩ ፖሊስ ሃይል አማካኝነት በመንደሩ ውስጥ የሶማሌ ባንዲራ በመስቀል የመንደሩ መስተዳድር በጅጅጋ ስር መሆኑን በመግለጻቸው የተነሳ ልዩው ፖሊስ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ጦርነት እንደገጠመ ከሞያሌ ያነጋገርናቸው ሰዎች ተናግረዋል።

የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ በከፈተው ውጊያ ከባድ መሳሪያ ላውንቸር፣ባዙቃና መትረየስ [PKM] መጠቀሙን የቦረና ተወላጆች ለቪ.ኦ.ኤ የገለጹ ሲሆን እስከ ሐሙስ እኩለ ቀን ድረስ የነበረው የማቾቹ ቁጥር 12 መድረሱንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ከሞያሌ ከተማ 140 ኬ.ሜ ርቀት ላይ የመከላከያ ሰራዊት ወታዳራዊ ካምፕ [በተለምዶ አጠራር መቶ አርባ]ያለና በክፍለ ጦር ደረጃ ብዛት ያለው ሰራዊት ያቀፈ ሆኖ ሳለ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ጦርነት ሲናሳ በዝምታ ከማየት በስተቀር ጣልቃ ገብቶ እንዳላስቆመ ሁሉ በአሁንም ግጭት ምንም አይነት ጣልቃ ገብነትን እርምጃ እንዳልወሰደ ነዋሪዎቹ ከአቶ አዲሱ አረጋን ቃል በሚቃረን መልኩ ተናግረዋል።

ከሞያሌ ከተማ ነዋሪ የሆነውና የቦረና ጎሳ ተወላጅ የሆነው አቶ ጉዩ ሃላኬ እረቡእ ንጋት ላይ ጀምሮ እስከ ሐሙስ ለሊት ድረስ እየተካሄደ ስላለው ጦርነትና የመከላከያ ሰራዊቱን ሚና በተመለከተ “የዞን 5 ልዩ ፖሊስ ገሪዎችን አስታጥቀው በጫሙ፣ጎፋ፣ቀያ መንደሮች የኦሮሚያን ባንዲራ በማውረድ የሱማሌን ክልል ባንዲራ ሰቀሉ። ከዚህ በፊትም መሬቱ የእኛ ነው እያሉ ለመውረር ብዙ ግዜ ግጭት ከፍተው እየተዋጋን መልሰናቸዋል። ዛሬም ህዝቡ ባንዲራቸውን በማውረድና እነሱንም በማባረር ውጊያ ገጥሟል” ያለ ሲሆን አክሎም “የፌዴራሉ ሰራዊት ለገሪዎቹ መሳሪያ በመስጠት ጦርነቱን የሚያዩ ናቸው።ግን የእኛ ወገን[የቦረና ማለቱ ነው] ሃይል አመዝኖ ማሸነፍ ስንጀምር ጣልቃ በመግባት አቁሙ ይሉናል” ሲል ተናግሯል።

የአቶ ጉዮ ሃላኬን የመከላከያ ሰራዊቱ ለሶማሌ ክልል ነዋሪዎች በተለይም ለገሪ ጎሳ ተወላጆች መሳሪያ ያስታጥቃል የሚለውን አባባል ለማረገጋጥ ከገለልተኛ ወገኖች በኩል ማግኘት ያልተቻለ ቢሆንም አባባሉን ከበርካታ የቦረና ተወላጆች ዘንድ የሚደገፍ መሆኑን ግን ማረጋገጥ ተችሏል።

በሞያሌው ግጭት ሐሙስ ምሽት ድረስ የሞቱት ቁጥር ከ12 ወደ 15 ከፍ ማለቱን ከሞያሌ የደረሰን መረጃ ቢያመለክትም ከሌላ ወገን በኩል ስላልተገለጸ በይፋ ከመግለጽ ተቆጥበናል።

በምስራቃዊው የኦሮሚያ መንደሮች በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ባሌ በራይቱና ገልቢ መንደሮች በሱማሌው ልዩ ፖሊስ ሃይልና በአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደሮች መካከል በተመሳሳይ ሁኔታ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የመስተዳድሩ ባለስልጣን አቶ አዲሱ አረጋ ያመኑ ሲሆኑ ግጭቱ በሌላኛው የኦሮሚያ ዞን በሚኤሶ ከሁለት ቀናት በፊት ጀምሮ ግጭት መኖሩን ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

ምስራቃዊው የኦሮሚያ ድንበር ከአቻው ሱማሌ ጋር በሚዋሰንበት መንደሮች ከባቢሌ እስከሞያሌ ከፍተኛ ግጭቶች እየተካሄደ ሲሆን ግጭቱም በመንግስታዊ መዋቅር ሰልጥኖና ታጥቆ ባለው የዞን 5ቱ ልዩ የፖሊስ ሃይልና ምንም ስልጠናም ሆነ ትጥቅ በሌለው የኦሮሞ አርሶ አደር መካከል እንደሆነ ይታወቀል።

አቶ አዲሱ አረጋ በ1997ዓ.ም በጸደቀው የክልሎች ድንበር ማካለያ ህግ መሰረት በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ሁለቱ መስተዳድሮች በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ መስማማታቸውን እና ብሎም ስምምነቱን እየተገበሩ መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም ዛሬም በአስሮች የሚቆጠሩ ንጹሃን በተነሳ የእርሰበርስ ጦርነት ህይወታቸውን ሲያጡና ሲፈናቀሉ ማየትና መስማታችን እንደቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።