ሰሜን ኮሪያ የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ቴክኖሎጂዋንና ሳይንቲስቶቿን ስራ በፌሽታ አከበረች

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ባለፈው እሁድ በውጤታማነት የሞከሩትን የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ቴክኖሎጂና ሳይንቲስቶችን ብሔራዊ ጀግና አቀባበል በመስጠት ማክበራቸውን የዛሬይቱ ራሺያ [RT] ዜና ዘገበ።

ባለፈው እሁድ በሰሜን ኮሪያ የተሞከረው የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ሀገሪቷ ከ2006 ጀምሮ ለአምስት ግዜ ከሞከረቻቸው የኒውክሌር ሙከራዎች ሁሉ የላቀና ሃይለኛ ነው የተባለለት ሲሆን የጃፓኑ ጠ/ሚ ሺንዞ አቤ “Far more powerful than their nuclear tests in the past” ከባለፉት የኒውክሌር ሙከራዎቻቸው ሁሉ እጅግ በጣም የላቀ ሃይል ያለው ሲሉ የቴክኖሎጂውን አቅም የገለጹ ሲሆን ሳይንቲስቶች ደግሞ አሜሪካን በ1945 በሂሮሺማ ላይ ከጣለችው አቶሚክ ቦምብ አስር እጅ ይበልጣል ሲሉ ገልጸውታል።

የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ቴክኖሎጂ ውስብስብነትና ውድነት እንደሰሜን ኮሪያ ለዓመታት በማእቀብ የደቀቀች ሀገር ትሰረዋለች ተብሎ ያልተጠበቀ ቢሆንም የፒዮንግያንግ ኒውክሌር መሳሪያ ኢንስቲቲዩት ባካሄደው ከፍተኛ ጥናትና ጥረት በአህጉር ተሻጋሪ ባልስቲክ ሚሳይል [ICBM] ላይ ተገጥሞ ወደ ተፈለገው የዓለም ዳርቻ መድረስ የሚችል የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ መስራት በመቻሉ ነው የሀገሪቱ መሪ ብሔራዊ ጀግኖች ሲሉ ሳይንቲስቶቹን ብብሔራዊ ደረጃ ሊያመሰግኗቸው የቻሉት ሲሉ ጠበብቶች ይናገራሉ።

በፒዮንግያንግ መንገዶች ላይ ከግራና ከቀኝ ሕዝብ በተሰለፈበት ሳይንቲስቶቹ በግልጽ መኪና እንዲያልፉ ከተደረገ በኋላ ወደ ታላቁ ኪም ኢል ሱንግ መታሰቢያ መካነ መቃብር በመሄድ ሀገራቸው የተጎናጸፈችውን የቴክኖሎጂ ውጤት ገልጸውላቸዋል ሲል ዘገባው ያትታል።

ምሽት ላይ የፒዮንግያንግ ሰማይ በተለያየ ህብረ ቀለማት በደመቁ ሪችቶች የደመቀች ሲሆን ነዋሪዋም በአድናቆትና በብሔራዊ ስሜት ተሞልተው በሀገራቸው፣ በሳይንቲስቶቹና በመሪያቸው ላይ ያላቸውን ኩራትና ታማኝነት ሲገልጹ ታይተዋል ሲል ዘግቧል።

image

በእለቱ ፕሮግራሙ በሚተላለፍበት የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ “እንደ ጋንግስተር የሚያደርጋት ኢምፔሪያሊስቷ አሜሪካ በደጃፋችን ባሉት አጋሮቿ አንዳች ጥቃትም ሆነ ትንኮሳን በሰሜን ኮሪያ ላይ ከቃጡ በአህጉር ተሻጋሪው ሚሳይላችን ላይ ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ጠምደን ምድራቸውን ዶግ አመድ እናደርጋለን” ብሎ ሲያስተላልፍ ተደምጧል።

ፒዮንግያንግን የህልውናዬን መሰረት ማስጠበቂያ ስትል በጣም የተማመነችበትንና የኮራችበትን ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ የሰሩትን ሳይንቲስቶች በወታደራዊ ሰልፍ፣ ማርሽና እና መዝሙሮች አጃቢነት በዜጎቿም ደማቅ አድናቆት አሰጣጥ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጀግና ስያሜን አጎናጽፋቸዋለች። ከፖለቲካዊ እይታና አቋም ነጻ የሆኑ ሳይንቲስቶች፣ ወታደራዊ ጠበብቶችና ዲፕሎማቶች የእሁዱን የፒዮንግያንግን የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ስኬታማ ሙከራን ሀገሪቷን ከኒውክሌር ማህበር ያስገባ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው ሲሉ በመናገር ዋሽንግተን ሰሜን ኮሪያን እውቅና በመስጠት ከማቀፍ በቀር ሌላ አማራጭ የላትም ቢሉም ትራምፕ መራሹ መንግስት ግን ያንን ሀቅ ከመቀበል ሞትን የሚመርጥ ሆኗል ሲሉ ይደመጣሉ።