በአማራ ግዛት ሕዝብና ባለስልጣናት ተፋጠዋል-ጎንደርና ጎጃም ለዓመጽ ተነስቷል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በአማራው ግዛት ያለው ውጥረት ከመቼውም ግዜ በላይ መክረሩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን በሰሜን ጎንደር በወልቃይት ጠገዴ የተፈጸመው እና በቅማንት ስም እንዲፈጸም የተወጠነው ውጥን በህዝቡና በባለስልጣናቱ መካከል ክፍተኛ ቅራኔ በመፍጠሩ ነው አካባቢው በውጠረት የከረረው ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአማራ መስተዳድርና በትግራይ ክልል መስተዳድር መሪዎች የወልቃይት፣ ጠገዴና የጠለምት ጥያቄ በስምምነት ፈተናል ተብሎ በመንግስታዊዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ከተገለጸበት ጀምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ወጣቶች የአከባቢውን ባለስልጣናት በእኛ ላይ ክህደት ፈጽማችሁ አሳልፋችሁ ሸጣችሁናል በሚል በግልጽ እንዳወገዟቸውና ህዝቡን ለመብቱ እስከ ህቅታው እንዲታገል ጥሪ ማስተላለፋቸውን መረዳት ተችሏል።

ከቀናት በፊት አቶ ገዱ ተሳታፊ በሆኑበት ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር ተካሄደ በተባለው የድንበር ውሳኔን የሰሜን ጎንደር ህዝብ ብቻ ሳይሆን የጎጃም ህዝብና የአጠቃላይ አማራ ህዝብ አለመቀበሉን በተወካዮቹ በኩል በግንባር ላለው የሰሜን ጎንደር ህዝብና ሽማግሌዎች በመላክ ማሳወቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።ሂደቱ በአማራው ግዛት ውስጥ ያሉትን የብአዴን ባለስልጣናትና ካድሬዎችን ክፉኛ ያስደነገጠ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በጎጃም የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ንብረታቸውን በመሸጥም ሆነ ዘግተው በመተው ከአካባቢው ሲርቁ እየታየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የህወሃት መራሹ መንግስት ቀደም ብሎ በጎንደርና ጎጃም በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የፖሊስ ጥበቃ ይሰጥ በማለቱ የአማራ ክልል ፖሊስ መምሪያ ለተወሰኑ የትግራይ ተወላጆችን በፖሊስ ጥበቃ ስር ማዋል መጀመሩ ተነግሯል።

በሰሜን ጎንደር የቅማንትን ማንነት ጥያቄን በመስከረም 7 ቀን 2010 በ12 ቀበሌዎች ውስጥ ህዝበ ውሳኔን ለማካሄድ ተወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በመቶ የሚቆጠር ህዝብ ያለቀበትን የወልቃይት ጠገዴና የጠለምትን ጉዳይ የአማራው መስተዳድር ያለምንም ምክክርና ከህዝብ ጋር ውይይት ከመቀሌ አቻው ጋር ተስማምቶ መስጠቱ የአካባቢውን ሕዝብ ክፉኛ እንዳስቆጣው ነው መረዳት የተቻለው።

በመንግስት በኩል ይነሳል ያለውን ህዝባዊ ዓመጽ ለመግታት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአግዓዚ ሰራዊት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በባህርዳር፣ በጎንደር አፍስሶ ከፍተኛ ፍተሻና ጥበቃ እያካሄደ እንዳለም መረዳት ተችሏል።

ሆኖም ውጥረቱ በጎጃም ይበልጥ ከሮና አይሎ ተገኝቷል። ሕዝቡ የብአዴን
አመራሮችንና የትግራይ ጋፊዎችን እንቅልፍ ነስቷል። ባህርዳር፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ ያሉ የትግራይ ባለሀብቶች ቤታችን ማን ይግዛን እያሉ ነው። አንዳንዶቹ እቃቸውን እየጫኑ ወደ ትግራይ ሲጓዙ እየታየ ሲሆን የህወሃትና የብአዴን ካድሬዎች ከተለመደው ስራቸውና እንቅስቃሴያቸው ሲቀሩ እየተያ መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።