በኦሮሚያና በሱማሌ ልዩ ፖሊስ ጦርነት ከ160 በላይ ሚሊሺያዎች ተገድለዋል ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ከእረቡእ ንጋት ጀምሮ ሐሙስ ቀኑን ሙሉ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል በሱማሌ መስተዳድር ልዩ ፖሊስ ሃይልና በኦሮሞ አርሶ አደሮች መካከል በተካሄደ ከባድ ውጊያ ከ160 በላይ ልዩ ፖሊስ ሚሊሺያ መገደላቸውን ኦምኒ [OMN] የአካባቢ ምንጮችን ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን የማቾቹን ቁጥር በማወቅ ደረጃ ከገለልተኛ ወገን ለጊዜው ማጣራት አልተቻለም።

ሆኖም የኦሮሚያ መስተዳድር የመገናኛ ጉዳዮች ምኒስትር አቶ አዲሱ ነገራ ለቪ.ኦ.ኤ ራዲዮ በሰጡት ቃል በሞያሌና በባሌ ክፍተኛ ውጊያ መከፈቱን ገልጸው የሞቱትን ሰዎች ቁጥር መረጃ ገና እያሰባሰቡ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወቃል።

የኦምኒ [OMN] ምንጮች ከሞያሌ ወደ አራባ የሚጠጉ፣ በባሌ ራይቱ ከሰላሳ አምስት በላይና በወሊገላ ደግሞ ወደ ሰማኒያ የሚጠጉ የሶማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል እንደተገደሉ የገለጹለት ሲሆን በኦሮሞ አርሶ አደር በኩል የሞተና የቆሰለ ቢኖርም ቁጥሩን ሳይገልጹ ቢያልፉም በሁለቱም ወገን በሶስቱ ግንባሮች ከመቶ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ይገምታሉ።

ምስራቅና ደቡባዊ ምስራቅ ኦሮሚያ ከሞያሌ እስከ ባቢሌ ባሉት መንደሮች ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል ጋር በግዛት ይገባኛል ውዝግብ ከፍተኛ ውጊያ የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ በመቀጠል ሰሞኑን ላለፉት ሁለት ቀናት ተከታታይ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑ ይታወቃል።