አርበኞች ግንቦት ሰባት በአለም የሚገኙ አባላቱን ለጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱ ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ከጳጉሜ 1 ቀን 2009ዓም ጀምሮ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ድርጅት ከአባላቱ ጋር ጠቅላላ ስብሰባ እያደረገ እንደሆነ ተገለጸ።

በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአላማችን ክፍል የሚኖሩ አባላቱ በድርጅቱ የትግል እንቅስቃሴ ላይ ለመምከር እንደተሰባሰቡ ለመረዳት ተችሏል።

ይህ ድርጅት በጥምረት ከተመሰረተ ከ2014 እኤአ ጀምሮ እንዲህ ያለ ጠለቅ ያለና በይዘቱም ሰፋ ያለ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ ለመጀመሪያ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

ጥር 2 ቀን 2014 እኤአ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና ዲሞክራሲ ግንባር መካከል በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት ይህ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ግንባር መመስረቱ ይታወሳል።

በዚህ የንቅናቄው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ከመጡ አባላት በተጨማሪ በበርሃ በትግል ካሉ የሰራዊት አባላት ተወካዮች እንደተካፈሉ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

ድርጅቱን በሊቀመንበርነት እየመሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በስብሰባው ለተገኙ አባላት ንግግር ማድረጋቸውም ተዘግቧል።

ለነጻነትና ለእኩልነት የሚደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግልን በረሃ ድረስ በመውረድ በመቀላቀል እየመሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ድርጅታቸው ባሳለፍነው ሁለት አመታት የተጓዘበትን ጎዳና ሲያብራሩ መደመጣቸውም ታውቋል።

መላ ኢትዮጵያን ከባርነት ከጭቆና እንዲሁም ከግፍ ነጻ ለማውጣት ድርጅታቸው በሚያደርገው ተጋድሎ ያጋጠመውን ውጣ ውረድና እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሊቀመንበሩ ለተሰብሳቢው አስረድተዋል።

በህውሃት የበላይነት የሚመራው ገዢው መንግስት በህዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን የመብት ረገጣ፣ አፈና እና ግድያን ከምድረ ኢትዮጵያ ለማስወገድ በሚደረገው ትንቅንቅ ድርጅታቸው እየደረገ ያለውን ተግባራትም ፕሮፌሰር ብርሃኑ በስብሰባው ለተገኙ አባላት አብራርተዋል።

በዚህ ጉባኤ የአርበኞች ግንቦት ሰባት መላው መዋቅር በጥልቀት እንደሚፈተሽና አስፈላጊ ተብሎ የታመነበትን ማሻሻያ የድርጅቱ አባላት እንዲጠቁሙና ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ እንደሚጠበቅ ከውስጥ የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህ ንቅናቄ እንደተፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ እንቅፋት የሆኑትን ድርጅታዊ ችግሮችን በነቂስ እንደሚወያይበትና መራራ የሆነውን የነጻነት ትግሉንም በማፋጠን ዳግም ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከመከራና ከባርነት ለማላቀቅ በሚረዱ መፍትሄዎች ላይ አባላቱ እንደሚመክሩ ከሚደርሱን መረጃዎች መረዳት ተችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጉባኤው መጠናቀቅ በፊት አዳዲስ አመራሮችን የመምረጥና የማጽደቅ ሂደትም ሊካሄድ እንደሚችልም እየተነገረ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ሊቀመንበር የሆኑት መኮንን ተስፋዬ በእንግድነት ተጋብዘው ንግግር እንዳደረጉም ታውቋል።

በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው የህውሃት አገዛዝ በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ውርደትና ግፍ እንደሚቃወሙና አገዛዙ መላው የትግራይን ህዝብ እንደማይወክል ሊታወቅ እንደሚገባ የትህዴኑ ሊቀመንበር አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ መደመጣቸውንም ምንጮቻችን ጠቅሰውልናል።

በዚህ በኤርትራ እየተካሄደ ባለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አርቲስት ሻምበል በላይነህ እንደተገኘና በስብሰባው መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የጀግንነት ዜማዎችን ለተሰብሳቢው ሲያንቆረቁር እንደነበረም ለመረዳት ተችሏል።

የጉባኤው ታዳሚዎችን ስሜት የቀሰቀሰና መሳጭ መሆኑ የተነገረለት “የፍጻሜ ትግል” በሚል ርእስ በአርበኞች ግንቦት ሰባት አደራ የኪነት ባህል ቡድን የተዘጋጀ ድራማም በጉባኤው መክፈቻ ቀርቧል።

በህዝባዊ አመጽ እየተናወጸ ያለውን የህውሃት አገዛዝ እድሜን ለማሳጠርና ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም ትግሉን በድል ለመቋጨት የሚረዱ ድርጅታዊ ለውጦችን የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በዚህ የጠቅላላ ጉባኤ ፍጻሜ ላይ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አዳዲስ አመራርን የመምረጥ ሂደትና የትግሉን አቅምና ፍጥነት የሚያጎለብቱ ልዩ ልዩ ስልቶችን ከዚህ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ድርጅቱ ይወስዳቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ ጉልህ ድርጅታዊ ለውጦች መካከል ይገኛሉ።