የተባበሩት መንግስታት በአፍሪቃ ስደተኞች ጉዳይ የአውሮፓ ህብረትን ክፉኛ መተቸቱ ተገለጸ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪቃ በተለያዩ ምክንያት ተሰደው ወደ አውሮፓ የሚመጡትን ስደተኞን ለማስቆም እያደረገ ያለውን ሂደት የተባበሩት መንግስታት በጽኑ መኮነኑ ተዘገበ።

ጦርነትን፣ የአምባገነን መሪዎች ቅጣትን አሊያም ድህነትን በመሸሽ ወደ አውሮፓ የሚፈልሱትን አፍሪካውያንን ለማስቆም በቅርቡ በፈረንሳይ አስተናጋጅነት የአውሮፓ ሃያላን አገሮች ሲመክሩ መሰንበታቸው ይታወሳል።

የሊቢያ፣ የኒጀርና የቻድ መሪዎች በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ግብዣ በዚሁ ስብሰባ እንዲካተቱ የተደረጉ ሲሆኑ የጀርመን መርሃ መንግስት አንጌላ መርክል፣ የጣሊያንና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ከፍተኛ ዲፕሎማትም እንደተገኙ ይታወቃል።

አውሮፓውያን በስደተኛ ጉዳይ ላይ ከነዚህ የአፍሪቃውያን መሪዎች ጋር የሚያደርጉትን ስምምነት የሰብአዊ መብት ጥሰትን እንደመደገፍ ይቆጠራል የሚል አስተያየት በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚስተር ዛይድ ሰጥተዋል።

ከምንም በላይ ስደተኝነትን በተመለከተ ከሊቢያ ጋር የሚደረግን ስምምነትን ወይም ትብብርን ኮሚሽነሩ በጽኑ ተችተዋል።

ስደተኞች በሊቢያ ባህር በር ለተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጋለጣቸውን የአውሮፓ ህብረት ጠንቅቆ እያወቀ እንዲህ አይነቱን ስምምነት ለመፈጸም መቻሉ ኮሚሽነሩ በተጨማሪ ኮንነዋል።

አውሮፓውያን የአፍሪቃ ዜጎች በስደት ወደ አውሮፓ እንዳይመጡባቸው ባላቸው ፍላጎት የተነሳ በአፍሪቃውያን ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ የሰብአዊ  መብት ጥሰት ላለማየት ሆን ብለው አይናቸውን እየጋረዱ እንደሆነም ድንበር የለሹ ህክምና ቡድን አስታውቋል።

በሴፕተምበር 24 ቀን 2017 እኤአ አገር አቀፋዊ ምርጫ የምታካሂደው የአውሮፓ ጠንካራይቱ ጀርመን ይህ የስደተኛ ጉዳይ ለምርጫ በሚፎካከሩ ፓርቲዎች መካከል ዋንኛ የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኖ ተግኝቷል።

ይህን በስደተኛ ጉዳይ የተጋጋለውን ክርክር ተከትሎ የጀርመን የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አገራቸው ለስደተኞች የምትሰጠውን እርዳታና ድጋፍ ዳግም ማጤን እንዳለባት አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

እንደሚንስትሩ ገለጻ በጀርመን አገር የሚገኙ ስደተኞች የሚያገኙት የመንግስት ድጋፍ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ለስደተኞች ከሚሰጡት ድጋፍ ጋር ሲነጻጻር ከፍተኛ እንደሆነ በማስረዳት መንግስታቸው ይህንን ድጋፍ መቀነስ እንዳለበት ጠቁመዋል።