የከፍታ ዘመን (በቴድ አበጋዝ)

0

የሀገር ከፍታ እዩት ተከበረ
ወገኔ በርሀብ አንጀቱ እያረረ
የሚበላው የለው ጦሙን አየዋለ
ዛሬ እሞት ነገ እሞት እያሰላሰለ።

መላቅጡ ጠፍቶት የሚሄድበቱ
መራብ ብቻ ሆኗል ሁሉም በየቤቱ
የምግብ ረሃብ የፍቅር ርሃብ የሃገር ርሃብ
ኧረ ሰው በስንቱ መከራ ይንገብገብ።

አገር እንደሌለው እየተሰደደ
ወገን በሰው ሃገር እየተዋረደ
በደቡብ አፍሪካ ዜጋ በሳት ነዶ
በሊቢያ ወገን እንደ እንሰሳ ታርዶ
በየመን ከጀልባ ወደ ባህር ሲጣል
በሳውዲ ምድር ላይ መከራ ሲቀበል
ኧረ ለመሆኑ አለሁልህ የሚል ያገር መሪ የታል።

ሰው በሃገሩ ላይ በትውልድ ቤቱ
እየተሰለለ ከሗላ ከፊቱ ሲመረመር ያድራል አመለካከቱ
በሃገሩ ጉዳይ ያገባኛል ካለ ከስራ መባረር
አልያም መታሰር ወህኔ ቤት መወርወር።

በሐሰት ምስክር እያጪበረበረ
ሲሻው በሃይማኖት ሲመቸው በጎሳ እየከፋፈለ
የኢትዮጵያ ገዥ በስንቱ ግፍ  ሰራ ለስንቱ ግፍ ዋለ።

ለ25 ዓመት ህዝብ አንገቱን ደፍቶ
እንዳይነጋገር ክልል ተበጅቶ
ለ10 ተከፍሎ በጎሳ ድሪቶ
መሰቃየት ብቻ አንድም ፍትህ ጠፍቶ።

አክራሪ ነፍጠኛ ጠባብ በሚል ስድብ መብቱ ታፍኖ
ፍትህ የጠየቀ መልሱ ዱላ ሆኖ
የከፍታ ዘመን እናክብር እያሉ
ላይሳካላቸው ሰውን ሊያታልሉ
ግራ የገባቸው መሪ ነን የሚሉት ይቅበዘበዛሉ።

ካለም ተርታ ወርደን አንድነት ተነፍግን
እያስተዳደሩን እንደባሪያ ዘመን
በድህነት ስቃይ በርሃብ እየነጎድን
በዘር ተከፋፍለን በጎጠኞቺ ትዕዛዝ መከራ አየበላን
ህዝብ እየተራበ አለማፈራቸው ሚሊዮን አውጥተው የከፍታ ዘመን አከበርን ሲሉን።

እውነት እላለሁ እናክብረው ካሉ አሁን የሚያከብሩት
የተዋረድንበት ሃገር የሞተበት
ህዝብ መብት አጥቶ አንገት የደፋበት
ዝቅ ዝቅ ከፍታ ወደሗላ ማደግ የሚከበርበት
አነርሱም ያክብሩ ህዝብም ያልቅስበት።