በሜክሲኮ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 90 አሻቀበ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ባሳለፍነው ሃሙስ በሬክተር መለኪያ  8.1 የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ በሜክሲኮ ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ውድመት ማድረሱ ታውቋል።

በዚሁ የመሬት መንቀጥቀጥ ወደ 90 የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ቢያመለክቱም ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ፍርሃትም እንዳለ ተዘግቧል።

ሜክሲኮን የመታት ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በአገሪቱ የመቶ አመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅና በአደገኛነቱም በመጀመሪያ ደረጃ ሊመዘገብ መቻሉንም ከሪፖርቶች መረዳት ተችሏል።

በደቡባዊ ሜክሲኮ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ህንጻዎች፣ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት በአደጋው ለደረሰው የህይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሃዘን በትዊተር በመግለጽ በመሬት መንቀጥቀጡ የተቋረጠው የኤሌትሪክ ሃይል እስከሚጠገን ድረስ ዜጎች ትእግስት እንዲኖራቸውም ተማጽነዋል።

በሬክተር ስኬል 8.1 እንደሆነ የተነገረለት ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ 15 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ያለ ኤሌትሪክ ሃይል እንዳስቀራቸው የተለያዩ ሚዲያዎች በዘገባቸው ገልጸዋል።

በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እስከ ዋናዋ ከተማ ድረስ እንደተሰማና ነዋሪዎችም በድንጋጤ ከነሌሊት ልብሳቸው በእኩለ ሌሊት በመንገድ ላይ ሲሯሯጡ መታየታቸውን ሮይተርስ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።