ቢዮንሴ በሃሪኬን ሃርቪ ለተጠቁ የምግብ እርዳታ ስታደርግ ዋለች

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ታዋቂዋ አርቲስት ቢዮንሴ በሂውስተን ቴክሳስ በመገኘት በሃሪኬን ሃርቪ ለተጠቁት ህዝቦች የምግብ እርዳታ ስታደርግ መዋሏ ተዘገበ።

የቀድሞው ዴስቲኒ ቻይልድ የሙዚቃ ባንድ ባልደረባ የሆነችው ሜሼል ዊሊያምስም በዚህ የእርዳታ ተግባር ላይ ከቢዮንሴ አጠገብ ተገኝታ እንደተሳተፈች የወጡ የቪዲዮ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቢዮንሴ በዚህ የቴክሳስ ክፍል ለ400 የሃሪኬን ተጠቂዎች የሚሆን የምግብ እርዳታ የሚውለውን ወጪ እንደሸፈነችም ተነግሯል።

አርቲስቷ በተጨማሪም በጎርፉ ምክንያት ቤት አልባ ለሆኑት ግለሰቦች በቅዱስ ዮሀንስ ቤተክርስቲያን በመገኘት ንግግር ማድረጓም ታውቋል።

ከቤዮንሴና ከሚሼል በተጨማሪም የተለያዩ አርቲስቶችና ታዎቂ ግለሰቦች በሃሪኬን ሃርቪ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚውል እርዳታ እያደረጉ ይገኛሉ። ጃኔት ጃክሰንም በዚሁ ተመሳሳይ ቦታ በመገኘት በጎርፉ የተጠቁትን ሰዎች መጎብኘቷና ንግግር ማድረጓም ተዘግቧል።

ኮመዲያን ኬቪን ሃርትም በበኩሉ በሃሪኬን ሃርቪ ጉዳት ለደረሰባቸው ማህበረሰብ የሚሆን የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርጉ የሙያ ባልደቦቹን ጠይቋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሃሪኬን ሃርቪ ጉዳት ለደረሰባቸው የድጋፍ ፓኬት የሚሆን የ15 ቢሊዮን ዶላር የመንግስት እርዳታ ፍቃድ የሚጠይቅ ሰነድ ባሳለፍነው ሳምንት መፈረማቸው ይታወሳል።