አልሸባብ በሶማሊያ የጦር ሰፈር በፈጸመው ጥቃት 30 ወታደሮችን መግደሉን አሳወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የአልሸባብ ሸማቂያን በኬኒያ ቦርደር አጠገብ በሚገኝ የሶማሊያ ወታደር ሰፈር እና የፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ተዘገበ።

በአልቃይዳ ይደገፋል በተባለው አልሸባብ ቡድን በደረሰው በዚህ ጥቃት በትንሹ ወደ ስምንት የሶማሊያ ወታደሮች ህይወታቸውን እንዳጡም የመንግስት ባለስልጣን አሳውቀዋል።

አልሸባብ በበኩሉ በዚሁ በተቀነባበረ ጥቃት በሱማሌ መንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንና ከ30 በላይ የመንግስት ወታደሮችን መግደሉንም ተናግራል።

በፈንጅ የተጠመደ ተሽከርካሪን በመንዳት የጦር ካምፑን ለመስበር የቻለው የአልሸባብ ቡድን ቁጥራቸው የበዛ ታጣቂዎችም በእግር በመግባት በመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃቱን እንዳደረሱት ባለስልጣናት ገልጻዋል።

በበለድ ሃዋ በተባለው ቦታ የተፈጸመው ይህ የአልሸባብ ጥቃት ከሶማሊያ ወታደሮች አልፎ ንጹሃን ዜጎችንም ለጉዳት መዳረጉም ታውቋል።

የአልሸባብ ተዋጊዎች ከጦር ሰፈሩ ጥቃት በተጨማሪ አንድ የፖሊስ ጣቢያንም እንዳጋዩት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንም እንኳን የአፍሪቃ ህብረት ከ18,000 በላይ ወታደሮችን በሶማሊያ ቢያሰማራም የአልሸባብን ጥቃት ግን ማስቆም እንደተሳነው ተንታኞች አስተያየታቸውን ገልጸዋል።