ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ጎባ ዞን ከ 5 ሺህ በላይ የሚገመቱ የሲዳማ ተወላጆች ተፈናቅለው በደቡብ ጭሪ ወረዳ ፈሰው እንደሚገኙና በሺዎች የሚቆጠሩ በየጫካው በመንገድ ላይ መሆናቸው ታወቀ

0

በምስራቅ ባሌ ዞን  በሚገኙ 14 ቀበሌዎች  ዉስጥ የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር በመቀላቀል በአምስት ቀበሌ ዉስጥ ከረጅም ግዜ ጀምሮ በጋራ በመተሳሰብ እና በመዋለድ ከሚኖሩበት ቦታ ዛሬ የኦሮሚያ  ክልል የትዉልድ ቦታችሁ አይደለም ተብለዉ እንደተፈናቀሉ የተፈናቃይ ቤተሰቦች ተናገሩ።

የዞኑ የየወረዳዉ አስተዳዳሪዎች፣ የቀበሌዎች ሹማምንቶች፣ የህዋት የቅርብ ደጋፊዎች በየክልልሉ ከሚገኙ እና በጥቅም ከተሳሰሩ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር የሲዳማ ተወላጆቹ ከሚኖሩባቸዉ ሰርድያ፣ ሔሮሳልፍ፣ ቡሉጥ ሁሩፋ፣ ቁምቢ እና ሐንጌዱሀም በመባል ከሚታወቁ ቀበሌዎች ዉስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ በተደረገዉ እና ጭካኔ በተሞላበት እንቅስቃሴ ዉስጥ ዋና ተዋንያኖች መሆናቸዉን ጨምረው ተፈናቃዮቹ ጠቅሰዋል።

እስከ አሁን ከሰርድያ እና ከሔሮሳልፋ ቀበሌዎች ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ሲቀሩ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የሲዳማ ተወላጆቹ አካባቢዉን ለቀዉ እንዲወጡ ሲደረጉ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉት በደቡብ ክልል ለኦሮሚያ ባሌ ጎባ ዞን አዋሳኝ ወደሆነችዉ ወደ ጭሪ ወረዳ ለመግባት ችለዋል።

ቁጥሩን ለመገመት አዳጋች የሆነ በሺዎች የሚቆጠር ቤተሰብ በየጫካዉ በጉዞ ላይ የሚገኙ መሆኑን፣ ከባሌ ጎባ ዞን ወደ ደቡብ ክልል ጭሪ ወረዳ ለመድረስ ከሶስት እስከ ስድስት ቀናት እንደሚፈጅ፣ በእድሜ ለገፉ አረጋዊያን፣ ህፃናትን ይዘዉ ለሚጓዙ ሴቶች እና ለህፃናት መንገዱ እስከ 10 ቀናት ሊፈጅ እንደሚችልም ተፈናቃዮቹ  ለዝግጅት ክፍላችን ከሰጡት መረጃ ለማወቅ ችለናል።

የሲዳማ ክልል መስተዳርር  ተሰደዉ ለመጡት ተፈናቃዮች የሚጠለሉበት ሸራ ከመስጠት እና አነስተኛ መጠን ያለዉ  ለእርዳታ የተላከ የነቀዘ ስንዴ ከማደል ዉጭ ለተፈናቃዮቹ በቂ ምግብ እና ዉሀ ማቅረብ እንዳልቻሉም የዓይን እማኞች ተናግረዋል። የእርዳታ አሰጣጡም በሶስት ዙር ከገቡት ስደተኞች  መሀከል የመጀመሪያ ለሆኑት እና ነሀሴ 30 ቀን ለገቡት አንድ እራስ የበቆሎ እሸት ለሁለት እንዲካፈሉ እየተደረገ እንደነበር ገልፀዋል።

በእቅዱ መሰረት  ከቀሩት ሶስት ቀበሌዎች ዉስጥ የሚኖሩት የሲዳማ ተወላጆች እንዲፈናቀሉ ከተደረገ ባማካኝ ወደ ሰላሳ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ለስደት እና ለረሀብ አደጋ እንደሚጋለጡ ከስደተኞቹ መሀከል ከአነጋገርነው ግለሰብ መረዳት ችለናል ።