በሞያሌ አካባቢ ከፍተኛ እልቂት የታየበት ጦርነት ዙሪያ የቀረበ ዘገባ-ከሱማሊያ የመጡም ተሳትፈዋል ተብላል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ እረቡእ እለት ከሱማሌ ዞን በመጡ አቶ አህመድ በተባሉ የኦሮሞ ተወላጅ ነጋዴ ከኬኒያ ሞያሌ[ጋምቦ]5ሚሊዮን የኬኒያ ሽንልግ ከኬኒያ ንግድ ባንክ አውጥተው ወደ ሳለ በገሪ ተወላጆ በሆኑ ሰዎች ይገደላሉ።

አቶ አህመድ በናይሮቢ ካሊፎሪኒያ ሰፈር ነዋሪና የአርሲ ተወላጅ ነጋዴ ሲሆን የሶስት ልጆች አባት እንደሆነም ለማወቅም ተችላል። የግድያው ይዘት ተራ ዘረፋ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በሞያሌ በኩል በሚካሄደው የንግድ ዝውውር ላይ የበላይነትን የያዙት የይወሃት ፓርቲ አባላት፣ደጋፊዎችና አጋሮቻቸው እንደሆኑ የሚታወቁት የገሪ፣ቡርጂና ገርባ ጎሳዎች በአንድ በኩል ሆነው በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ[ቦረና]አማራ፣ጉራጌ ተወላጅ ነጋዴዎች ላይ የሚደረግ የበላይነት ጥቃት አካል ነው ሲሉ የአካባቢው ሰዎች በተለይ ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።

የሆነው ሆኖ የአቶ አህመድ በገሪ ተወላጆች መገደል ከቦረና ተወላጆች በኩል የአጸፋ እርምጃ አስወስዶ ወደ አጠቃላይ ውጊያነት በመቀየር በሁለቱም ወገን በመቶ የሚቆጠር ሰው ያለቀበት ውጊያ የተከሰተ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ያጠናቀርነው ልዩ ዝርዝር ዘገባ እንደሚከተለው ቀርባል።
**ሞያሌው ጦርነት ከሱማሊያ ጭምር የመጡ ተዋጊዎች ተሳትፈውበታል ተብላል።

በዛሬው የሰኞ ውሎ-አካባቢው በፌዴራል ሰራዊት ተጥለቅልቃል። አሊ መሀመድ በሞያሌ ክልል 5 ነዋሪ የሆነ የገሪ ተወላጅ ነው። ስለ ዛሬው ሁኔታ ሲናገር “የፌዴራል ሰራዊት በአጠቃላይ ጦርነት የተካሄደባቸውን ወረዳዎች ተቆጣጥሮ በየሜዳው የወደቀን የኦሮሞ እሬሳ እያሰለቀመ ነው ያለው።” ያለ ሲሆን በጡርነቱ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ “አይደለም ከቦረና በኩል የሞቱትን ብዛት ለማወቅ ይቅርና በእኛ በገሪዎች በኩል የሞቱትን እንካን ገና ቆጥረን አላወቅንም። ግን በቦረና በኩል የሞቱት ከመብዛታቸው የተነሳ እሬሳ እንካን መሰብሰብ አቅታቸው ጥለው እስከመሸሽ ደርሰዋል።ያንን እሬሳ ነው ዛሬ ፌዴራል እያሰበሰበ ያለው” ሲል ተናግራል።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በተከፈተ ጦርነት በሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሃይል ጥቃት በጫሞ እና ጎፎ ቀበሌዎች የክልል 5 ባንዲራ ተሰቅሎ የነበረውን ለማንሳት በቦረና በኩል ህሙስና ዓርብ በተወሰደ መልሶ ማጥቃት ከ30በላይ የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል የተገደሉና ከቦረና በኩልም ወደ 15የሚጠጉ በተገደሉበት ውጊያ ቀበሌዎቹን መልሰው በኦሮሚያ አስተዳደር ስር ማድረጋቸው ይታወቃል።

ሆኖም ከዓርብ ለሊት ጀምሮ እስከ እሁድ በተካሄደ ከባድ ውጊያ በሁሉቱም ወገን በአስሮች የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች ካለቁበት በሃል የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል አጠቃላይ ወረዳዎቹን መልሶ የተቆጣጠረ መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በጦርነቱም ገሪዎች ከሱማሌ ድረስ የመጡ የሱና አል ወል ጀማ 400ተዋጊዎች ተሳትፈውበታል ሲሉ የቦረና ተወላጆች ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።
መሰረቱን በማእከላዊ ሶማሊያ ያደረገው ሱና አል-ወልጀማ የሚባለው የሱማሊያ ተዋጊ ሃይል በህወሃት መራሹ መንግስት አል-ሸባብን ለመወጋት ተብሎ የተቃቃመና የሚበጀተውም በኢትዮጵ መንግስት ሆኖ በሞቃዲሾ መንግስት እውቅና ያለው አጋዥ ሃይል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ በሞያሌና በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ውጊያ ተሳታፊ እንደሆነ ከቦረና ተወላጆች በኩል ተደጋግሞ ተገልጻል።

በሞያሌ የኦሮሚያ ዞን ነዋሪ የሆነው ገልገሎ ገልማ ስለግጭቱ ሲናገር”ገሪዎች ከሱማሌ ከመጡ ሽፍቶችና ከፌዴራሉ ሰራዊት ጋር ሆነው ህዝባችንን ፈጁት።የሞቱብንን ብዛት ገና አላወቅንም።መሬቱንም ፌዴራል ተቆጣጥሮት መልሶ ለሶማሌዎቹ አስረክባል።የሶማሌው ልዩ ዞን የሚዋጋው እጅግ በተደራጀ ከባድ የጦር መሳሪያ ሲሆን ፌዴራሉ ግን በእጃችን ያለውን ክላሽ እንካን ለማስፈታት ዘመቻም እያካሄደ ነው ” ሲል ይናገራል።
ሰሞኑን ውጊያ ሲካሄድባቸው የነበሩት ጫሞ፣ጎፎ፣ኡደት፣መልካ፣ቦርቦር፣መልገሌ የሚባሉ ቀበሌዎች ሁሉ ዛሬ በፌዴራል ሰራዊት ስር ሆነው የሶማሌ ዞን አስተዳደር ተመድቦላቸው እንዳሉ ለማወቅ ተችላል። ሆኖም በቦረና ተወላጆች በኩል የተነገረውን የሱማሌ ሃይሎች ከማእከላዊ ሱማሊያ መጥተው መሳተፍን በተመለከተ የገሪው ተወላጅ አሊ መሀመድ “እኛ [ገሪዎች ማለቱ ነው] በማን አልተረዳንም። እንዲያውም የክልላችን ልዩ ፖሊስ በቂ ሃይል ስላልመደበልን እስከመጋጨት ደርሰናል።የኦሮሞ ተዋጊዎች እኮ ከሻሸመኔ ድረስ በመጡ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ሃይል ልብስ እያስለወጡ የተሳተፉበት ውጊያ ነው የገጠመን ” ሲል ይናገራል።
ባለ ሁለት ቀበሌዋ ሞያሌ በሁለት ክልላዊ መስተዳድሮች ኦሮሚያና ሱማሌ ተከፍላ ያለች ሲሆን በሱማሌ ዞን ነዋሪ የሆኑት ገሪዎች በኬኒያና በሱማሊያ ተሰራጭተው የሚኖሩና በድንበር ተሻጋሪ እርሰበርስ ትብብራቸው የሚታወቁ እንደሆነ ይታወቃል።
በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ መንደሮች ላይ ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በሱማሌ ልዩ ፖሊስ ሃይልና በኦሮሞ አርሶ አደሮች መካከል በተካሄደ ድንበር ወለድ ግጭት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት የጠፋበትና ከፍተኛ ንብረት የወደመበትን ግጭት ለመፍታት የሁለቱ መስተዳድር ፕሬዚዳንቶች ተፈራርመዋል ተብሎ መገለጹ አይዘነጋም።
ወደ ሞያሌ ልመልሳችሁና-ሁለቱም ወገኖች የኦሮሞና የሱማሌ ዞኖች ህዝብ በፌዴራሉ ሰራዊት ጦርነቱን ከማስቆም ይልቅ በማባባስ ተግባሩ ሲገልጹ የተደመጡ ሲሆን እንደ ገልገሎ አገላለጽ ደግሞ “ፌዴራሉ ጦርነቱ እንዳይከሰት ማድረግ እየቻለ በዝምታ ካየ በሃላ የእኛ ሰው በርትቶ መሬቱን መከላከል ሲጀምር ለሱማሌው ልዩ ፖሊስ ድጋፍ ከመስጠቱም በላይ የእኛን ሰዎች ሃላ ቀር ክላሽ ጠብመንጃ ለማስፈታት አሰሳ ማድረጉ የሚያሳየው ግልጽ አቃሙን ነው” ሲል ይገልጻል።
በሞያሌ ከተማ ፍርሃት መንገሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። አስከፊ እልቂት የታየበት ጦርነት ከከተማው በ11ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የተካሄደ ከመሆኑም በላይ የሁለቱም ወገኖች በከተማዋ ውስጥ በአንድ አውራ መንገድ ተለይተው በመፋጠጥ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ጦርነቱ ወደ ከተማዋ ይገባል ሲሉ በስጋት ተወጥረው ነው ያሉት።
የጦርነቱን ቀጣና ለግዜው ፌዴራሉ መቆጣጠሩን የገለጹ ሲሆን “ህዝቡ ጫካ የገባ በመሆኑና ፌዴራሉ የገሪን እና የቦረናን ሽማግሌዎች ሰብስቦ ጦርነት እንዳይካሄድ ስላላስታረቀ በማንኛውም ሰዓት ጦርነቱ ሊነሳ ይችላል “ሲል የገሪው ተወላጅ አሊ ተናግራል።

መቀመጫውን ጂጂጋ ያደረገውና በነውጠኛው አብዲ ኢሌ የሚመራው የሱማሌ ዞን መንግስታዊውን ልዩ የፖሊስ ሃይል በመጠቀም ከምስራቅ ኦሮሚያ ባቢሌ እስከ ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ሞያሌ ድረስ የተስፋፊነትን ወረራ እያካሄደ ሲሆን በኮሎኔል ገብሬ እንደሚመራም ይነገራል።