በግብጽ የአይ ኤስ ሚሊሻዎች በወሰዱት እርምጃ 18 ፖሊሶችን መግደላቸው ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በግብጽ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ በተከፈተ ጥቃት ወደ 18 የፖሊስ ሰራዊት አባላት መገደላቸውና ሌሎችም መጎዳታቸው ተዘገበ።

በሰሜናዊ ሲና በተፈጸመው በዚህ ጥቃት አራት የወታደር ተሽከርካሪዎች በቦምብ ተመትተው ሲወድሙ ሌላ አምስተኛ ተሽከርካሪ በፍንዳታው ምክንያት በእሳት መንደዱ ተገልጿል።

በዚህ ጥቃት ህይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል ሁለት ከፍተኛ መኮንንኖች እንደነበሩ ሲታወቅ ከተጎዱት ውስጥ አንድ የፖሊስ ብርጋዴር እንደሆነም ተዘግቧል።

ለዚህ በአይነቱና በይዘቱ ከባድ ለተባለለት ጥቃት አይ ኤስ መሉ ሃላፊነቱን እንደሚወስድም አሳውቋል።

ባሳለፍነው እሁድ የግብጽ ፖሊስ 10 የአይ ኤስ ተጠርጣሪዎች የተባሉ ግለሰቦችን በካይሮ መግደሉን ማስታወቁ ይታወሳል።

የግብጽ ፖሊስ በእነዚህ 10 ግለሰቦች ላይ በካይሮ የወሰደው እርምጃ ምንአልባት ለዛሬው ጥቃት መንስኤ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል።

ከ2013 እኤአ የመሃሙድ ሙርሲ ከፕሬዝዳንትነት በሃይል መውረድ ተከትሎ ግብጽ በተከታታይ በአይ ኤስ ታጣቂዎች ኢላማ መውደቋም ተዘግቧል።