አርበኞች ግንቦት 7 እያካሄደ ባለው ጉባኤው የንቅናቄውን ድርጅታዊ መዋቅርና የመተዳደሪያ ደንብ ፈትሾ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዳደረገ ታወቀ

0

ጉባኤውን ከጀመረ ጥቂት ቀናትን ያስቆጠረውና ኤርትራ ውስጥ የመጀመሪያው ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከሁለት ቀን በፊት ከውህደቱ ወዲህ የነበረውን የድርጅቱን መዋቅርና የመተዳደሪያ ደንብ በዝርዝር አንድ በአንድ ሲፈትሽ ከዋለ በኋላ መሰረታዊ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲደረግ መወሰኑን ከንቅናቄው አካባቢ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ከተዋሃደ ወዲህ ስራ ላይ የነበረው የድርጅቱ መዋቅር በሶስት ምሶሶዎች ላይ የቆመና መልካምድራዊ ቅርጽ የነበረው አደረጃጀት ተቀናጅቶና ተናቦ በተቀላጠፈ መንገድ ትግሉን ከዳር ለማድረስ ያልታሰቡ ተግባራዊ ተግዳሮቶችን ፈጥሮ መቆየቱን በመረዳት እንዲሁም ከዕለት ወደዕለት እያደገ የመጣውን የሕዝቡን የነፃነት ትግል ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የነፃነት ትግሉን ከዳር ለማድረስ እነዚህን ችግሮች አስወግዶ በተቀላጠፈና በተሳለጠ መንገድ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የሚአስችል የማሻሻያ ድንጋጌዎችን በሙሉ ድምጽ እንዳጸደቀ ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ስትራቴጂውን በተመለከተ ንቅናቄው እየተከተለ ባለው ሁለገብ ትግል ህዝባዊ እምቢተኝነትን፣ ህዝባዊ ተጋትሮንና ህዝባዊ ሻጥር ስልቶችን አቀናጅቶ በመተግበር በጠመንጃ ኃይል ህዝባችንን እስከወዲያኛው ባሪያ አድርጎ ለመግዛት እየተንቀሳቀሰ ያለውን የወያኔ አገዛዝ ለማስወገድ  ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ ለመታገል የሚአስችል ነው ተብሏል።

ጉባኤው በቀጣዮቹ ቀናት በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን ካስተላለፈ በኋላ ንቅናቄውን ለቀጣዩ 3 ዓመታት በብቃት ሊመሩ ይችላሉ ብሎ በእውቀታቸው፣ በችሎታቸውና በልምዳቸው እምነት የሚጥልባቸውን አመራር ዓባላት በዲሞክራሲያዊ መንገድ መርጦ እንደሚጠናቀቅ ከጉባኤው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።