በምስራቅ ኦሮሚያ ባለስልጣናት ታግተው ተገደሉ-በጉርሱም ሕዝብ ተቃውሞውን አሰማ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በምስራቅ ኦሮሚያ ጉርሱም ወረዳ ከሱማሌ ዞን በመጡ ልዩ ፖሊስ ሃይል ሶስት ባለስልጣናት ታግተው ሁለቱ ሲገደሉ አንደኛው ያመለጠ ሲሆን የአካባቢው ሕዝብ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ምድር እየተካሄደ ያለው ግድያ ይቁም በማለት ሰልፍ መውጣቱን የቪ.ኦ.ኤ ድምጽ ዘግቧል።

የጉርሱም ወረዳ የጸጥታ ክፍል ምክትል ሃላፊ አቶ ሞሀመድ አብዱራህማን፣ የጉርሱም ወረዳ የቀድሞ አስተዳደር አቶ ሀሰን መሀመድ እና በኦሮሚያ አድማ በታኝ ሃላፊ የነበረ አቶ አብዱል ጀባል ከጉርሱም ወደ ሀረር ሲጓዙ ቦምባ ላይ በሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ለሊቱን ሁለቱ ሲገደሉ አንደኛው አቶ ሞሀመድ አብዱራህማን ለማምለጥ ባደረጉት ጥረት ገደል ገብተው የእግር ስብራት ደረሶባቸው ህክምና ላይ እንዳሉ ከስፍራው ተዘግቧል።

ካለፉት ሁለት ሳምንት ጀምሮ በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ምድር ከሱማሌ ዞን አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተነሳው ጦርነት በምስራቅ በኩል ተባብሶ የተገኘ ሲሆን በተለይ በጉርሱም እና አከባቢው ወረዳዎች በኦሮሞ አርሶ አደሮችና በሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል መካከል ለ4 ተከታታይ ቀናቶች የዘለቀ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጦርነቱ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ እየተገለጸ ባለበት ሁኔት የማቾቹን ቁጥር ለይቶ ለማወቅ እንዳልተቻለም የተገለጸ ሲሆን የሱማሌው ዞን ልዩ የፖሊስ ሃይል እያደረገ ያለውን የወረራ እርምጃ በማውገዝና የፌዴራሉ መንግስት ወረራውን እንዲያስቆም የሚጠይቅ ሰልፍ ማክሰኞ እለት በጉርሱም መካሄዱን መረዳት የተችሏል። በአንጻሩም የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ በሰልፈኞቹ ላይ በመቶኮስ ማቁሰል መቻሉ ከስፍራው ተዘግቧል።

በተለይም በሱማሌ ዞን ልዩ የፖሊስ ሃይል ታፍነው ከታሰሩ በኋላ በእስር ቤት ውስጥ የተገደሉት የሁለቱ ባለስልጣናት ሁኔታ የጉርሱምን ሕዝብ በማስቆጣት ለተቃውሞ ሰልፍ እንዳበቃው መረዳት የተቻለ ሲሆን ሕዝቡ በሶማሌው ልዩ ፖሊስ ሃይል የተከፈተበትን ጥቃት በማውገዝ ገዳዮቹን መንግስት ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥያቄ ቢያቀርብም የኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን የተቃረበውን ተቃውሞ ለመበተን ተኩስ መክፈቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ክልል መገናኛ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ የተጠቀሰውን ጦርነት እና የባለስልጣን ታግቶ መገደል እውነት መሆኑን አምነው ድርጊቱ በሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል እንደተፈጸመ የገለጹ ሲሆን የሱማሌው ዞን አቻቸው አቶ እድሪስ እስማኤል ሀሰት ነው በማለት ማጣጣላቸውን ከቪ.ኦ.ኤ ዘገባ ማወቅ ተችሏል።

ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ባላቋረጠ ከፍተኛ ጦርነት ስር መሆናቸውን የገለጹት የጉርሱም እና አካባቢው ወረዳ ነዋሪዎች ጦርነቱ በመንግስታዊ ደረጃ እጅግ በታጠቀው የሶማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል በኩል የተከፈተባቸው ወረራ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን በፌዴራሉ መንግስት እና በመከላከያ ሰራዊቱ በኩል የተደረገ እርምጃ እንደሌለም ተናግረዋል።

በምስራቅ ኦሮሚያ በባቢሌ ወረዳ ዋጪሌ፣ ጎፋ፣ ሰላድመያ የተባሉ መንደሮች በሰሞኑ ተከታታይ የውጊያ ቀጠናነታቸው የተጠቀሱ ቢሆንም ግጭቱ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በባሌ ራይቱ ዞን፣ በጉጂ አርሲ ነገሌ ዞን እና በሞያሌ አከባቢ ባሉ መንደሮች በተከፈተ ጥቃት በአስሮች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ማወቅ የተቻለ ሲሆን በፌዴራሉ በኩል ግጭቱን ለማስቆምና ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ እርምጃ እንዳልተወሰደም ነዋሪዎች መግለጻቸው ተሰምቷል።