የኦሮሚያ ባለስልጣን የሱማሊያን ጦር ተሳታፊነት አጋለጡ-ከጦርነቱ ጀርባ ያለው እጅ?

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር መገናኛ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል ከሱማሊያ በመጡ ተዋጊዎች እየተረዳ ውጊያ እያካሄደብን ነው ሲሉ የተማረከን ወታደር መታወቂያ ይፋ በማድረግ ያጋለጡ ሲሆን ጂጂጋ ያለው አቻቸው አቶ እድሪስ እስማኤል ደግሞ ማስተባበላቸውን ቪ.ኦ.ኤ ገለጸ።

በደቡባዊቷ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ አቅራቢያ ሰሞኑን በተካሄደው ውጊያ የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል ከማእከላዊ ሱማሊያ የመጡ የአል-ሱና-አል-ወልጀማ የተባሉ ተዋጊዎችን እንዳሰለፈ ቀደም ሲል አባይ ሚዲያ የሞያሌ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን ድርጊቱንም ማክሰኞ እለት በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር የመገናኛ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በድጋሚ የተማረከን ምርኮኛን በማስረጃነት በመጥቀስ ድርጊቱን በይፋ አጋልጠዋል።

የቪ.ኦ.ኤዋ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣን አቶ አዲሱ አረጋን እና የሱማሌ ክልል ባለስልጣን የሆኑትን አቶ እድሪስ እስማኤልን በተናጠል ባነጋገረችበት ወቅት አቶ እድሪስ የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል አንድም ቀን የኦሮሚያን ግዛት አልፎ ጥቃት ፈጽሞ እንደማያውቅ በመግለጽ ጋዜጠኛዋን “የሰማሽው ሁሉ መቶ በመቶ ውሸት የሆነ ፈጠራ ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም “የኦነግና የጁሃር ጸረ ሰላም ሃይሎች በሱማሌ ዞን ወረራ ፈጽመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ እያካሄዱ ያሉት እነሱ ናቸው። የእኛ ህዝብ በራስ መከላከል ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በምስራቃዊና ደቡባዊ ምስራቅ ኦሮሚያ ምን እየተካሄደ ነው ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን በርካታ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ሲሆን በተለይም ከሱማሊያ ማእከላዊ ግዛት ድረስ ተዋጊ ሃይል አምጥቶ እየተዋጋ ያለው የሱማሌ ዞኑ ልዩ ፖሊስ ሃይልና በኦሮሚያ መስተዳድር በኩል በጉዳዩ ላይ እየተወሰደ ያለውን አቋምና እርምጃን የሚመለከተው ልዩ ጥንቅር እንደሚከተለው ቀርቧል።

***የጦርነቱ መንስኤና ዋና ዓላማ በሁለቱም ክልሎች የተለያየ ሆኖ እንዴት ሊገለጽ ቻለ? ከኦሮሚያና ሱማሌ ዞን ጦርነት ጀርባ ያለው ሃይልና ዓላማ ማነው?

አቶ አዲሱ አረጋ የሱማሊያ መንግስት መከላከያ ሰራዊት አባል የሆነውን ሻለቃ ሹኔ ኬሮው አብዲ [Shune Kherow Abdi.Rank Maj] በሞያሌ ግንባር ተማርኮ ይፋ ያደረጉት ተዋጊ በሱማሌ ዞን አስተዳደር ከማእከላዊ ሱማሊያ ተጠርተው ከመጡት ወደ 400 የሚጠጉ የአል-ሱና-አል-ወልጀማ ተዋጊዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ወደ 300 ያህሉ ጎፋ እና መቶ ያህሉም ዋጪሌ እንደተሰለፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

image

አል-ሱና-ወልጀማ መቀመጫውን በባይዶዋ ባደረገውና በኢህአዴግ መንግስት በሚደገፈው የሱማሊያው የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ መሪነት የሽግግር መንግስት ተመስርቶ ወደ ሞቃዲሾ ለመግባት በሚዘጋጅበት ወቅት እንደ ደጋፊ የውጊያ ክንፍ ተብሎ በገዢው የኢትዮጵያ መንግስት የተመሰረተ ተዋጊ ሃይል ሲሆን በ2006ቱ የኢህአዴግ ሱማሊያን ወረራ የሞቃዲሾውን እስላማዊ ፍርድ ቤት [Islamic Court] ሃይሎችን በመዋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ሃይል ነው።

አል ሱና-ከስነ አፈጣጠሩ እስከ የዛሬ ህልውናው የህወሃት መራሹ መንግስት በኢትዮጵያ ከፈጠራቸው ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ከህነው ኦ.ህ.ዴ.ድ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ድርጅት ሲሆን በሱማሊያ የኢህዲግ ቅርንጫፍ ተብሎ ከ”ሀ” እስከ “ፐ” ያለውን ድርጅታዊ አወቃቀር፣ አመራር፣ በጀትና ዓላማን ከህወሃት ተነድፎለት የሚንቀሳቀስ በሱማሊያ የህወሃት ድርጅት የሆነ ሃይል ነው።

በደቡባዊና ማእከላዊ ሱማሊያ ግዛት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአልሸባብ ቁጥጥር ነጻ ያወጣቸውን ግዛቶችን እንዲያስተዳድርና እንዲጠብቅ ሃላፊነትና ግዳጅ እየተሰጠው የሚወጣው አል-ሱና ወልጀማ ድርጅት በሞቃዲሾ ያለውን የፌዴራል መንግስት በተዋጊ ክንፍነት እንዲያገለግል በመደረጉ የፌዴራላዊት ሱማሊያ መንግስት የመከላከያ ሰራዊትነት ታቅፎ ግን በጅትና ትእዛዝን ከአዲስ አበባ እየተሰጠው በክልሉ የሚንቀሳቀስ ተዋጊ ሃይል ሲሆን በመካከለኛው ሱማሊያ ጁባና ጌዶ አከባቢ ብዙሃን ከሆኑት የኦጋዴን ጎሳ ተወላጆች የተውጣጣ ቢሆንም መሪሃን እና ገሪ የተባሉ ጎሳዎችንም አካቶ የያዘ ተዋጊ ክፍል ነው።

የኢትዮጵያ ሱማሌ ክፍል በአብዛኛው በኦጋዴን ተብሎ በሚጠራው የሱማሌ ጉሳ የተሞላ ሲሆን ይህ ጎሳ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በኬኒያና በሱማሊያ ሰፍሮ ያለ እንደሆነ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መወቃር ውስጥ አንደኛው የመንግስት ክፍል በሆነው የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ባለስልጣን አቶ አዲሱ አረጋ የእነዚህን ሱማሊያን መቀመጫቸው ያደረጉትን በሱማሊያ የህወሃት ድርጅት ቅርንጫፍ የሆኑትን አል ሱና ወልጀማ ተዋጊዎችን ከሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል ጋር ተሰልፈው በተለያየ የኦሮሚያ መንደሮች ውስጥ ጥቃት መፈጸምን በይፋ አጋልጠዋል።

ለምንድነው ህወሃት መራሹ መንግስት ቀለብ የሚሰፍርለትን እና የሚቆጣጠረውን የሱማሌን አል ሱና ሰራዊት በኦሮሚያ ላይ ለመጠቀም የፈለገው ብለን ልንጠይቅ ግድ ይለናል አንድ በህወሃት መራሹ መንግስት የሚደገፍና የሚመራ ተዋጊ ክፍል በኦሮሚያና ሱማሌ ዞን መካከል በተነሳው ግጭት ተዋጊ ሆኖ ስናገኝ።

የአቶ አዲሱ አረጋን አባባል የሱማሌ ዞኑ አቻቻው አቶ እድሪስ እስማኤል ሸምጥጠው በመካድና ግጭቱንም ጸረ ሰላም ሃይሎች የሆኑ “የኦነግና የጁሃር ሃይሎች ናቸው” ለማለት ለምን አስፈለጋቸው?

በትንሹ 15 ሺህ ከፍ ሲልም እስከ 30 ሺህ የሚቆጠረውን የሱማሌ ዞን ልዩ የፖሊስ ሃይል እርምጃ እና ወረራ ገዢው የህወሃት መንግስት ሳያውቀው በክልሉ ባለስልጣናት ብቻ የታዘዘ ሃይል ነውን ይህንን ሁሉ ወረራና ጥቃትን እየሰነዘረ ያለው?

አቶ እድሪስ እንዳሉት “የፌዴራሉ መንግስት ሰራዊት የትሄዶ ነው አል ሱና ከውጭ ድንበር ጥሶ ወደ ኢትዮጵያ የገባው” በማለት ለማጣጣል የተጠቀሙበት መከራከሪያ የአልሱና እና የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል በኦሮሚያ ግዛቶች ላይ የከፈታቸው ጥቃት በሙሉ በህወሃት መራሹ መንግስት ይፋዊ እውቅና ብቻ ሳይሆን ትእዛዝ ሰጪነት እየተካሄደ መሆኑን መግለጽ ቢቻልም ዋናው ዓላማም ከመሬት የዘለለ ሌላ ጉዳይ ይኑረው አይኑረው ማስቀመጥ አይቻለን ይሆናል።

ከህወሃት መራሹ መንግስት እውቅና እና ፍቃድ ውጪ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ዜጎቻን ለመውጋት የሚያበቃ ምክንያቱም፣ ሞራልና ብቃቱም የሌላቸው የአል ሱና ወልጀማ ተዋጊዎች መገኘት በኦሮሚያና በሱማሌ ዞን መካከል ሳያቋርጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጀርባ ትልቁ የህወሃት እጅ እንዳለበት በማያሻማ መንገድ ምስክር ሆኖ ሲያሳየን መረዳት ይቻላል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት ጦርነቱ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሳይሆን በሱማሊያው ልዩ ፖሊስና በሰፊው የኦሮሞ አርሶ አደሮች መካከል ሲሆን ሂደቱም መንግስታዊ ዓላማና ትእዛዝ ያለው ነው ብለን እንድናይ አድርጎናል።