ሰሜን ኮሪያ ለአሜሪካ ወዮልሽ ስትል አሜሪካ ደግሞ ቻይና ላይ ዛተች

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አዲስ ማእቀብ በሰሜን ኮሪያ ላይ በአድ ድምጽ ባጸደቀ ማግስት ፒዮንግያንግ ለዋሽንግተን “በታሪክሽ አይተሽውም ሆነ ደርሶብሽ የማያውቀውን ታላቅ መከራና ስቃይ ሰጪ ህልውናሽን እስከማጥፋት የሚደርስ ቅጣት ይሰጥሻል” ስትል ከባድ ዛቻ የሰነዘረች ሲሆን አሜሪካ ደግሞ በበኩሏ የተላለፈውን ማእቀብ ቻይና የማትተገብር ከሆነ በቤጂንግ ላይ የተናጥል ማእቀብ ልትጥልባት እንደምትችል የሚያሳስበውን ማስጠንቀቂያ የዛሬዪቱ ራሺያ [RT] ዜና ጣቢያ ዘገበ።

ከሳምንት በፊት ሰሜን ኮሪያ ካደረገችው የሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ ስኬታማ ሙከራ በኋላ የጸጥታው ምክር ቤት በአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጠያቂነት አስቸካይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን በኮሪያ ልሳነ ምድር እየተካሄደ ስላለው ውዝግብ መክሮና ሰሜን ኮሪያንም አውግዞ በሁለት ሳምንት ግዜ ውስጥ ሁለተኛ የተባለውን አዲስ የኢኮኖሚ ማእቀብ በፒዮንግያንግ ላይ ማስተላለፉ ይታወቃል።

አዲሱ ማእቀብ ሰሜን ኮሪያ በዓመት ከ720 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የምታገኝበትን የጨርቃጨርቅ ምርቶቿን ወደ ውጭ እንዳትሸጥ፣ ለኒውክሌር መስሪያነት ያገለግላል ያሉትን የነዳጅ ድፍድፍ እንዳታስገባና የተጣራም ነዳጅ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን በርሜል በላይ እንዳታስገባ [የአሜሪካ እለታዊ የተጣራ የነዳጅ ፍጆታ ከ6 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነው] የሚያግድ ሲሆን ይህንንም ደንብ በተላለፈ ማንኛውም ሀገር ላይ አሜሪካ በተናጥል ማእቀብ እና ቅጣት እንደምትጥልባቸው ማስታወቋ ይታወቃል።

ሆኖም ማእቀቡ በተመ.ድ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ በኩል የቀረበውን እና እጅግ ጠንካራ፣ ሃይለኛና ታሪካዊ የተባለውን ረቂቅ በራሺያና ቻይና እምቢ ባይነት ማስተላለፍ ባለመቻሉ አሁን የተላለፈው ማእቀብ የተፈለገውን ተጽእኖ በማድረግ ፒዮንግያንግን ኒውክሌር መሳሪያ አያስፈታም የሚለውን እምነት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንኳን ተቀብለው ሲያስተጋቡት ተደምጠዋል።

ሆኖም ማክሰኞ እለት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባለስልጣን እስቲቨን ኑቼን “ቻይና በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ የማታከብር ከሆነ አሜሪካ ቤጂኒግን በዓለም አቀፍ ገንዘብ ምንዛሪ [ዶላር ማለታቸው ነው] እንዳትጠቀም ከማገድ ጀምሮ አንዳችም የንግድ ልውውጥ ከቤጂንግ ጋር ባለማድረግ የሚቀጣ የማእቀብ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ግምጃ ቤት ባለስልጣን ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተሰጠን ትእዛዝ መሰረት የተደረገ ሲሆን 80% የሰሜን ኮሪያን የንግድ ሸሪክ የሆነችውን ቤጂንግን በማስገደድ ፒዮንግያንግ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እንደታሰበ ይገመታል።

በአሜሪካ እና ቻይና መካከል በዓመት ከ650 ቢሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ልውውጥ እየተካሄደ እንዳለ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን አሜሪካ በየዓመቱ በ350 ቢሊዮን ዶላር ተበልጣ [በሁለቱ ሀገሮች መካከል በሚካሄደው የንግድ ልውውጥ ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚሸጠው እቃ ከአሜሪካ ወደ ቻይና ከሚሸጠው በ350 ቢሊዮን ብልጫ ያለው ሆኖ ተገኝቷል] ያልተመጣጠነ የንግድ ልውውጥ ያላቸው ሀገሮች ሲሆኑ ቻይና በአሜሪካን ግምጃ ቤት የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ቦንድና ኖቶች ዋጋ ያለው ባለቤት እንደሆነችም ለማወቅ ተችሏል።

የቻይናን ባንኮች “ከእኛ ጋር ወይንስ ከሰሜን ኮሪያ ጋር መነገድ ትፈልጋላችሁ”ብለን እናማርጣቸዋለን የሚሉት የአሜሪካው ግምጃ ቤት ባለስልጣን ከፒዮንግያንግ ጋር የንግድ ልውውጥ በሚያደርጉ ማናቸውም የቻይናም ይሁኑ ሌሎች ሀገራት ድርጅቶች ሀገራቸው በተናጠል ማእቀብ ልትቀጣ መዘጋጀታቸውን ቢገልጹም ከቤጂንግ በኩል እስከ አሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

በሰሜን ኮሪያ በኩል የተጣለባት አዲሱ የተ.መ.ድ ማእቀብ ከኒውክሌር ቴክኖሎጂዋ ስንዝር ያህል ፈቀቅ እንደማያደርጋት በመግለጽ ውሳኔውንም “እርባነ ቢስ የኢምፔሪያሊስቶች ጥቃት” በማለት የገለጸችው ሲሆን በተለይ ለአሜሪካን ደግሞ The US will face the “greatest pain and suffering” and “permanent extinction” “አሜሪካን ህልውናዋ በምድር ገጽ በሚጠፋ መልኩ ታላቅ ስቃይና መከራን እንሰጣታለን” በማለት እጅግ ጥብቅና ጠንካራ ማስፈራሪያን ከዚህ በፊት አድርጋው በማይታወቅ ደረጃ በመግለጽ ለማእቀቡ አጸፋ መልስ ሰጥታለች።

በ1950ዎቹ በሁለቱ ኮሪያ ጦርነቶች ወቅት ቻይና አንድ ሚሊዮን ወታደሮቿን ከሰሜን ኮሪያ ጎን አሰልፋ የደቡብ ኮሪያ አጋር ከሆነችው አሜሪካ ጋር የተዋጋች ሲሆን 400 ሺህ ወታደሮቿም በኮሪያ ልሳነ ምድር መስዋእት እንዳረገች የሚዘነጋ አይደለም።

ከፒዮንግያንግ ጀርባ ያለችው ሌላዋ ሀገር ራሺያ ፕሬዚዳንቷ ቭላድሚር ፑቲን “የሰሜን ኮሪያ ህዝብ ሳር ቢሆን እየበላ የኒውክሌር ቴክኖሎጂውን ከመገንባት ወደ ኋላ የሚል ህዝብ አይደለም” በማለት ልችግሩ መፍትሄ ማእቀብና የሀይል እርምጃ ሳይሆን ሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂዋን የህልውናዋ ጉዳይ አድርጋ በመግለጽ እስከ ሃይድሮጂን ኒውክሌር ቦምብ [በአህጉር ተሻጋሪ ባልስቲክ ሚሳይል ላይ መገጠምና አሜሪካ መድረስ የሚችል] ድረስ መስራት የቻለች ሲሆን አሜሪካም ፒዮንጊያንግን እንደ አንድ ኒውክሌር ታጣቂ ሀገር እውቅና በመስጠት ከመቀበል ይልቅ አስፈታለሁ በሚል ግትር አቋማ በመጽናት ፒዮንጊያንግን ማስጨነቁን ገፍታበታለች።