የኬኒያ ተቃዋሚዎች የጠየቅነው ቅድመ ሁኔታ ካልተመለሰ ምርጫ የለም ሲሉ አስጠነቀቁ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ ተቃዋሚ ናሳ [NASA ] የኬኒያ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን [IEBC] ካልታደሰና ካልተስተካከለ የጥቅምቱ 17 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አይካሄድም ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን ገዢው የኢዮቤሊዩ [Jubilee] ፓርቲና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ተቃዋሚው ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ትቶ በምርጫው እንዲሳተፍ አሳስበዋል፡

የናሳ አመራር አባላት ዛሬ በሴናተር ሞሴስ ዋታንጉል ተናጋሪነት ለኬኒያዊያን እንዳስታወቁት 11 የምርጫ ቦርድ አመራር አባላት ከሃላፊነት እንዲነሱና አልጉራይ የተባለው የመራጮችን ድምጽ መስጫ ወረቀት የሚያትመው የህትመት ድርጅት ስራውን እንዳያከናውን የጠየቁ ሲሆን No accountability, No election ተጠያቂነት በሌለበት ምርጫ አይኖርም በማለት ይፋ አድርገዋል።

እንደ ተቃዋሚዎቹ አገላለጽ የጠየቁትና ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ በምርጫው እንደማይሳተፉ ሳይሆን የገለጹት ምርጫ የሚባል እንደማይካሄድና ይህንን መንግስት እንደሚያፈርሱ ነው ያስጠነቀቁት።

ሴናተር ሞሴስ ዋታንጉላ ከናሳ ፓርቲ መሪ አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ፣ ካሎንዞ ሙሶዮካና ዴቪድ ሙሰይላ ባሉበት [We are not boycotting the election but we are saying there is no election taking place if our conditions not addressed] የጠየቅነው ቅድመ ሁኔታ ካልተመለሰ በምርጫው አንሳተፈም ሳይሆን የምንለው ምርጫው እራሱ አይካሄድም እያልን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በናኩሩ በምረጡኝ ዘመቻ ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ሁሩ ኬኒያታ እና ምክትላቸው አቶ ዊሊያም ሩቶ በፍጥነት የተቃዋሚውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “ተቃዋሚው ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ትቶ በመጪው ምርጫ ላይ እንዲሳተፍ እንጠይቃለን” ያሉ ሲሆን የነሀሴ 8ቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ውድቅ ያደረገውን የሀገሪቷን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቋም ክፉኛ ሲያብጠለጥሉ ታይተዋል።

ትናንትና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለምክር ቤቱ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ተመራጭ የሆኑ ተቃዋሚ አባላትና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ዴቪድ ማራጋ ፕሬዚዳንቱ ምክር ቤቱን ለመሰብሰብ ስልጣን የላቸውም በማለት ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወቃል።