በሱማሌ ዞን ያሉ የኦሮሞ ተወላጆች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ በልዩ ፖሊስ እየተፈናቀሉ ነው ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በምስራቁ የኢትዮጵያ ግዛት በሶማሌ ዞን ልዩ የፖሊስ ሃይል በውጫሌና በጅጅጋ ከተሞች ነዋሪ የሆኑትን የኦሮሞ ተወላጆች በሃይል እያፈናቀለ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ የሚገልጽ ሲሆን የጀርመን ድምጽ በበኩሉ በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ሰዎች እየተፈናቀሉ ነው ሲል ዘግቧል።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ እስከአሁን የተፈናቀሉት ቁጥር ከ1 ሺህ እንደሚበልጥ የተገለጸ ሲሆን ማፈናቀሉ በምስራቅ ኦሮሚያ ሃይሎ መታየቱ ተገልጾ ዛሬ ከድሬዳዋ ከሐረር እና ጅጅጋ ይነሱ የነበሩ አገር አቋራጭ አውቶብሶች እና ሚኒባሶች በአጠቃላይ የትራንስፓርት አገልግሎቱ መቋረጡን የአካባቢውን ነዋሪ ምንጭ ጠቅሶ ጀርመን ድምጽ ዘግቧል።

በዚህም ምክንያት ከድሬዳዋ እስከ ጅጅጋ ያለው መንገድም የተዘጋ ሲሆን ዛሬ በሱማሌ ዞን የውጫሌና ጅጅጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በዞኑ ልዩ ፖሊስ ሃይል አስገዳጅነት ከፍተኛ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር የመገናኛ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በትናትናው እለት በኦሮሞ አርሶ አደር ላይ ጥቃትና ወረራ የከፈተው የሶማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል እንደሆነ ይፋ ያደረጉ ሲሆን ከማእከላዊ ሱማሊያ የመጣ ተዋጊ ሃይል በውጊያው ተሳታፊ የሆነበትን የተማረከ የሱማሊያ መንግስት ወታደርና በሻላቃ ማእረግ ያለን ምርኮኛን ዋቢ በማድረግ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በምስራቅ ሀረርጌ በባቢሌና በሂራሪ ዛሬ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን ሰልፈኛው የሱማሌውን ልዩ ፖሊስ ሃይል አውግዘዋል የፌዴራሉንም መንግስት ሴራ ሲያወግዙ ተደምጠዋል።

ሆኖም በኦሮሚያ ቄሮዎች በመላ ኦሮሚያ ለነገ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በዛሬው እለት በሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ምክንያት አስቸካይ እርዳታ ማድረስ በማስፈለጉ ለሌላ ግዜ አስተላልፈናል ሲሉ አስታውቀዋል።

የሱማሌ ዞን ልዩ ፖሊስ ሃይል በአቶ አብዲ ኢሌ የሚመራና ከ15-30 ሺህ በደንብ የተደራጁና የታጠቁ ተዋጊዎች ያሉበት ሃይል ሲሆን የገዢው ፓርቲ ህወሃት ጄኔራሎች የበላይነት የሚመራ ነው ተብሎ ይነገራል።