የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ተለውጧል (በአል አሚን አቡበከር)

0

ደርግ በመደብ ትግል እና የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም  በማስፋፋት ስም ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ እንዲገደል፣ እንዲሰደድ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅምና መብቱን እንዲነጠቅ ያደረገው የአማራውን ነገድ እንደሆነ ይታወቃል። በሌላ በኩል ደርግን እንዋጋለን፣ የየነገዳችን መሪ እንሆናለን፣ ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ብለው ጫካ የገቡ ቡድኖችም በአውራ ጠላትነት ፈርጀው የጥፋት እጃቸውን ያነሱት በአማራው ላይ ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ዘውዳዊ ሥርዓቱ፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖቱና የአማራው ነገድ ተያያዥና ተደጋጋፊዎች ነበሩ። ይህ ተደጋጋፊነትና ተባባሪነት እንዳይኖር ለያይቶ መምታት ያስፈልጋቸው ነበርና፣ ዘውዳዊ ሥርዓቱና ሃይማኖቱ ባንድቀን አዋጅ እንዲፈርሱ ሲደረግ፣ አማራው ብቻውን ቀረ። የሚገርመው አማራው ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ልጆቹ ምን ሊመጣና ሊከተል እንደሚችል ለማሰብና ከመጭ አደጋዎች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ዘዴ አልዘየዱም። አማራው በዘር ተልይቶ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመበት እያዩና እየሰሙም ለምን ያሉት እግጅ ጥቂቶች ናቸው። ይህም በመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ አማራው የመኖርና ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱን ተነፍጎ፣ በተገኘበት እየታደነ በመገደል ላይ ነው። ባለፉት 26 ዓመታት ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አማራ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ ተደርጓል። ይህ አልበቃ ብሎ የመዋለድ መብቱን በሕዝብ ዕድገት መቆጣጠሪያ ስም መካንና ታማሚ እያደረጉት ነው።

የመጀመሪያው በጠላትነት የፈረጀውን አማራውን ማጥፋት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው። ለዚህ ለሁለተኛው ግቡ፤ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊያን፣ እና ኢትዮጵያዊነት የሚሉትን ሁሉ መደምሰስ ነው። አሁን በኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ወይንም ሳትሆን፤ በመጀመሪያ ላይ ትግሬ፣ ቀጥሎ ደግሞ ኦሮሞ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ አኙዋክ እና አዲስ አበቤ ነው ያሉት። በእንጀራ ልጅነት ደግሞ አማራ አለ። እንግዲህ ኢትዮጵያዊ የለም ማለት ነው። ይሄን ደግሞ በተግባር፤ የትግሬዎቹ መንግሥት ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ሲያካሂደው ቆይቷል። ይህ ከአንድ ትውልድ በላይ የፈጀ ሂደት ነው። ይሄንን እንደሌለ ሰርዘን ወደፊት አንጓዝም፤ እንዳልነበረ ቆጥረንም፤ ወደኋላ ተመልሰን በምኞት ፈረስ የኋሊት ጋልበን፤ ከአእምሯችን አናጠፋውም።

ከሁሉም በላይ አማራው በብዛት የሚኖርባቸውን ጠቅላይ ግዛቶች ሕዝብ ፣ከዐማራው ውጭ ነኝ ወይም አገው ነን፣ ኦሮሞ ነን፤ እና ቅማንት ነን የሚሉትን ፣ከዐማራው በመነጠል የየራሳቸው አስተዳደር እንዲመሠርቱ አድርገዋል። ይህ ድርጊት ለነገዶችና ጎሳዎች ዕኩልነት ታስቦ ከሆነ፣ ሥራው መጀመር የነበረበት ትግራይ ውስጥ በትግሬዎች ለተጨቆኑት ኩናማዎች፣ ሣሆዎች፣ ኢሮጶች፣ አገዎች፣ አፋሮችና ኦሮሞች መሆን ነበረበት። ወያኔ የትግራይን ግዛት እስከ ቤንሻጉል ለማስፋት ባለው የቆየ የመሥፋፋት ዓላማ፣ ሰሜን ጎንደርን የግዛቱ አካል ለማድረግ ላቀደው ዕቅድ ተፈጻሚነት እንቅፋት ከጎንደር ሕዝብ እንዳይገጥመው በማሰብ ቀድሞ ቅማንቶቹን አደራጅቶ በፀረ-ዐማራው ግንባር ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እያደረገ ነው። በጎንደር አማራና በቅማንት ሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት ቅራኔና ልዩነት እንዳልነበር ማንም ያውቀዋል። ሆኖም የፀረ-ኢትዮጵያ ፍላጎት አስፈጻሚ በሆነው  ወያኔ ጥቅም የተገዙ ጥቂት የቅማንት ተወላጆች ጽሕፈት ቤታቸውን መቀሌ እና አዲስ አበባ ላይ አድርገው ወያኔ በሚሰጣቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ የጎንደርን አማራ አርዶ ጨርሶ የመሬቱ ባለቤት ለመሆን እየጣሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህ በቅማንትና በአማራ ሕዝቦች መካከል ሆን ተብሎ የተፈጠረ ችግር የሚጠቅም ከሆነ የሚጠቅመው ወያኔንና ግብረ አበሮቹን እንጂ፣ የቅማንትን ሕዝብ ሊሆን ከቶ አይችልም።

ስለዚህ በአሁኒቱ ኢትዮጵያ ያለው ዋናው ትግል፤ በማንነት ላይ የተመሠረተን በደል መቋቋም ነው። በተለይም ለአማራው፤ የአልሞት ባይ ተከላካይነት ትግል ነው። ይሄን ሀቅ መቀበል፤ በጊዜው መገኘት ነው። አሁን በኢትዮጵያ ያለው፤ የመደብ ትግል አይደለም ዋናውን ቦታ የያዘው። ይሄን የሀገራችንን የፖለቲካ ኡደት መቀበል የቸገረው፤ የአማራውን ትግል ሊረዳ አይችልም። ይህ የአማራው ትግል ወደየት ሊያመራ እንደሚችልም አይረዳውም። በርግጥ፤ ኢትዮጵያ እንዳትጠፋ ከሚል ጭፍን ፍላጎት ተነስቶ፤ የአማራውን ማንኛውም እንቅስቃሴ መኮነን የትም አያደርስም። እንደማንኛውም የኅብረተሰብ እውነታ ሁሉ፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት፤ ቆሞ የተገተረ ሀቅ ሳይሆን፤ የራሱ የሆነ ኡደት ያለው ተለዋዋጭ ነው። ይህ ይህ የመደራደሪያ ጉዳይ አይደለም። ይልቅስ የወቅቱን የፖለቲካ እውነታ መቀበሉ፤ ለነገ ለሚደረገው ዝግጅት መስመር ይከፍታል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ተለውጧል።