ቴላቪቭን እና ሃይፋን ወደ አመድነት እቀይራለሁ ስትል ኢራን በድጋሚ ዛተች

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

እስራኤል ቅንጣት ታክል ስህተት በኢራን ላይ ከወሰደች ቴህራን ቴላቪቮን እና ሃይፋን ወደ ትቢያነት ትለውጣለች ሲሉ የኢራኑ ጦር ሃይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄ/ል አብዱልራሂም ሞሳቪ መዛታቸውን የዛሬዪቱ ራሺያ [RT]ዜና ዘግባል።

እስራኤልና ኢራን እጅግ ሲተናኮሱ፣ሲካሰሱና እርሰበርስ ለመጠፋፋት ሲዛዛቱ የኖሩ ሀገራት ሲሆን እስራኤል የኢራን ጥንካሬና እድገት ለህልውናዪ ያሰጋኛል በሚል ጽኑ እምነት የቴህራንን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና የቴክኖሎጂ እድገታንም ለመገደብ ስትጥር ኢራን ደግሞ በበኩል በመካከለኛው ምስራቅ የአይሁዳዊው የእስራኤል መንግስት ህልውና ለክልሉና ለህልውናዪ ጠንቅ ነው ስትል የቴላቪቭ መንግስት መፍረስ አለበት ባይ ነች።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ በመሆን ከተመረጡ ሁለት ወርም ያልሞላቸው አዲሱ አዛዥ በአጭር ግዜ ቆይታቸው ትናንት ለሁለተኛ ግዜ በቴላቪቮ ላይ የማስጠንቀቂያ ዛቻ የሰነዘሩ ሲሆን ባለፈው ነሀሴ ውስጥ የአይሁዳዊው መንግስት ህልውና እጅግ ቢበዛ ከ25ዓመት በላይ አይፈጅም ሲሉ የእስራኤልን በጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠፊነትን ተናግረዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ከ2011 የዓረብ አብዮት መፈንዳት በሃላ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ለክልላዊ ስልጣን የበላይነት፣ለእምነትን መሰረት ላደረገ አይዲኦሎጂ የበላይነትና ብሎም ለዓለም ሃያላን የበላይነት መፋለሚያ መድረክ በመሆን አያሌ አዳዲስ ሃይሎችን እያስተዋወቀ ባለበት ወቅት ኢራን በሶሪያና በየመን የበላይነታን ለማጽናት ታላቅ ዘመቻን በምታጣጡፍበት ሁኔታ እስራኤልና ሰኡዲ ዓረቢያ በሌላ ወገን በጸረ ኢራን ግንባር ተሰልፈው በእጅ አዙር እየተፋለሙ እንደሆነ ይታወቃል።

ከራሺያ ጋር በመሆን በሶሪያ የምእራባዊያኑን የእጅ አዙር ጸረ አሳድ መንግስት ዘመቻን እየተዋጋች ባለችበት ሁኔታ ከእስራኤል ጋር እየተፋጠጠች እንዳለ የተነገረ ሲሆን ለሒዝቦላህ የሊባኖስ ሺዓ ተዋጊ ሃይል የላከችው የጦር መሳሪያም ለበርካታ ግዜ በቴላቪቮ ዓየር ሃይል እየተመታባት መውደሙ ይታወቃል።