ብሔር የሰፈረበት የሀገራችን የቀበሌ መታወቂያ ወረቀትና መዘዙ (በያሬድ አውግቸው)

ትላንት ሴፕቴምበር 18/ 2017 በቶሮንቶ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን የካናዳ መገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ    የሰብአዊ መብት ረገጣ ላይ  ዝምታቸውን ይስበሩ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ  አድርገን  ነበር። በሰልፉ ላይ በተደጋጋሚ ከሚነሱ መፈክሮች መካከል “ ኖ ሞር አናዘር ርዋንዳ” (No more another Rwanda)  አንዱ ነበር። የርዋንዳ መሰል እልቂት በድጋሚ እንዳይከሰት አንስራ  የሚል መልእክት አለው መፈክሩ። የርዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ስናስብ ደግሞ  800,000 የሀገሪቱ ዜጎች መታወቂያቸው ላይ የሰፈረው የጎሳቸው ስም እየታየ የታጨዱበት ግዜን  ያስታውሰናል። ዘራቸው በመታወቂያ ላይ  ባይሰፍር  ኖሮ የሟቾች ቁጥር እጅግ ዝቅ ይል እንደነበር መገመት ይቻላል።  በዋናነት  ግን ዘርን ማእከል ያደረገ አገዛዝ የዘረጋና ህይወት እንዲዘራ የሰራው የወቅቱ የርዋንዳ መንግስት ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

ዘረኛው የህወሐት ቡድን በበኩሉ የማእከላዊውን የመንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ  ከተገበራቸው እኩይ እቅዶች መካከል  ተመሳሳይ ጦስ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ብሄርን በመታወቂያ ላይ በግዴታ ማስፈር ይገኝበታል።   ላለፉት 26 ዓመታት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አስፈላጊነቱ ወይም ጥቅሙ እንዲገለጽላቸው በተደጋጋሚ  የጠየቁ ቢሆንም መልስ ሰጪ ግን አላገኙም።  ዘርህ እንዳይጻፍ ከፈለክ  መታወቂያ አንሰጥህም  የሚል የድፍረት መልስ ግን  ሲሰጥ ቆይቶአል፤ አሁንም ይህንኑ መልሳቸውን ቀጥለውበታል።  የጦሱን ጨረፍታ ግን ሰሞኑን በግልጽ አይተነዋል። በመቶዎች ተገድለው  ከሀምሳ ሺህ በላይ  የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል መታወቂያቸው እየታየ ሲባረሩ ማለታችን ነው።  መረጃው የለንም እንጂ ከኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ መልክ መታወቃቸው እየታየ የተባረሩ ሶማሌዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት እይከብድም።

እንግዲህ የቂምና ብሄር ተኮር ፖለቲካው ውጤት እየተመለከትነው እንገኛለን።  የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንቶች ሰሞኑን በጋራ በሰጡት  ጋዜጣዊ መግለጫ  በሁለቱ ክልል መካከል የታየው ዘር ላይ ብቻ ያተኮረ  ግጭት  ̋አስደንጋጭና ከባህል የወጣ ክስተት ̋ ብለውታል። ታዲያ ምን ሊያጭዱ ጠብቀው ነበር ? አስገራሚ  ሰዎች  ናቸው። አሁንም ከጥፋታቸው ለመማር ዝግጁነት አይታይባቸውም። በአጠቃላይ እንቅልፍ ላይ ናቸው። እንግዲህ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች መተላለቅ ላይ  ታላቋን የትግራይ መንግስት እመሰርታለሁ ብሎ መለያየትን ከዘረጋልን  ህውሃት  የወረስነው ይሄ ነው።  ድንዛዜ። ዝም ብሎ እንደ እንስሳ ወደ ሞት መጓዝ ። የመለስ ሌጋሲ ።

እንግዲህ የመታወቂያችን  ጣጣን በሰሞኑ በተፈናቀሉ ዜጎቻችን በጨረፍታ አይተነዋል።  እየሄድንበት ያለንበት መንገድ  ሀገሪቱን እንደ ግዜያዊ ቤቱ የሚያያት መሰሪው ህወሐት  ለጥፋታችን ያመቻቸልን መንገድ በመሆኑ በግዜ እንንቃ። ከአሁኑ ተምረን ዘረኝነት ይብቃን ካላልን  የእኛው እልቂት ከርዋንዳ የከፋ እንደሚሆን የምናያቸው ምልክቶች ያረጋግጣሉ። የድንበር ጭቅጭቁ ብዛት፣ በማህበራዊ ሜዲያዎች የምናያቸው የጥላቻ  ስብከቶች እንዲሁም   ቁጥር አንድ  ልዩነት ሰባኪዎች ምሁር ተብዬዎች መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል። ወደ አህምሮአችን እንመለስ። ፈልገን ባልተፈጠርንበት ብሄር ጭቅጭቁ ይቁም። አዎ ከእንስሳነት ባህርይ እንውጣ።