መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካ (በአል አሚን አቡበከር)

መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካ ትርፉ ያው መበተን ነው፡፡ እረኛ እንዳሌላቸው በጎች መቅበዝበዝ፤አቅጣጫው እንደጠፋበት ኮምፓስ ነፋስን መከተል! ነገር ግን ህዝብ ሁሉንም ያውቃል፡፡ ለህዝብ ልብ ልብ የሰጡ ሀገራት ዜጎቻቸውን ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆኑ አሸናፊ ማድረግ ችለዋል፡፡ በፖለቲካ ርእዮቶች መግባባት ሲያቅታቸው ባለመግባባታቸው ተግባብተው በህዝብ ጥቅሞች፤ ብልጽግናና ንቃተ ህሊና መዳበር ላይ ግን አብረው ለስኬቱ ይዋደቃሉ፡፡

እከሌ የሰራው ልብስ አይመጥነኝም አሊያም እሱ ስለነካው ብቻ አልለብሰውም አይሉም፡፡ ይደምቁበታል፡፡ ልዩነቶቻቸውን ደግሞ የአንደኛው እስኪያሸንፍ በአደባባይ ያታግሉአቸዋል፡፡ አሸናፊው ሲለይና ህዝብ ሲከተለው ውሁዳኑ እጅ መስጠታቸውን ያውጃሉ፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እነሱ ጋር የማይሰራ ኋላቀር ተረት ተረት ነው፡፡

እንዲህ ያለውን ልብና አመል በሰጠን ብዬ ተመኘሁ፡፡ ምኞቴ መሬት ጠብ አይልም ይሰጠናል፡፡ ያልፋን እንደሁ እንጂ ይሰጠናል፡፡ ዛሬም ሰከን ብለን ካጤናቸው ከእሴቶቻችን ብቻ በመማር የዚህ ሀገር ፋኖ የማንሆንበት ምን ምክንያት ይኖራል ስልም አሰብኩ፡፡ እኛም ሞኞቹ ዱላ አንስተን ስንከሻከሽ ሀገር መሽቶባት ማደሪያ ስታጣ ወዮታችን ራሱ ወዮ ነው፡፡ ወዲያም እድሜ ልኩን የህዝብ ወንበር ላይ ተጣብቆ መምሻውን ሀገሩን የሚያሻት ስንት ጉደኛም አለ፡፡ እልፍ ሲልም ከዚያችው ወንበር ስር ተወሽቆ የሚመራትን ሀገር ላብ የሚመጥ፤ ከነመሰሎቹ ጋር እየዶለተ የሚቸበችባትም እንዲሁ፡፡                                                                

በርግጥ የእብድ ገላጋዩ ብዙ ነው፡፡ የሚያቀብለንን ዲንጋይ እየያነሳን ሀገር ከገነባንበት ግን ጥል ሳይሆን ሰላም፤ መቃቃር ሳይሆን መወዳጀት፤ መቀማማት ሳይሆን የቄሳርን ለቄሳር የእግዜርን ለእግዜር በሚለው አስተሳሰብ የሚገባውን ለሚገባው በመስጠት፤ በመፈራራት ሳይሆን በተጨባጩ ዓለም በመተማመን የእኩልነት ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡