የዚምባቡዌው ሙጋቤ ዶናልድ ትራምፕን ጎሊያድ ሲሉ ተቹ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በኒው ዮርክ ተ.መ.ድ ጉባኤ ላይ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የዘመናችን ጎሊያድ ሲሉ ተናገሩ።

የ93 ዓመት አዛውንቱ ሙጋቤ በዓርብ እለቱ ንግግራቸው “አንዳንዶቻችን በዶናልድ ትራምፕ ንግግር ከማፈርና ከመሸማቀቅ አልፈን የፈራንም ሆነናል” ያሉ ሲሆን አክለውም “የመጽሐፍ ቅዱሱና ግዙፉ ጎሊያድ በዘመናችን ያውም በመካከላችን ያለ እስኪመስለን ድረስ የአንድን ሀገር ህልውና በአጠቃላይ እደመስሳለሁ እያለ ሲናገር ሰማነው” በማለት ማክሰኞ እለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን እንዳለ ከማውደም በስተቀር ሌላ አማራጭ የላትም” ሲሉ ለተናገሩት ቃል ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ፕሬዚዳንት ሙጋቤ “የመጽሐፍ ቅዱሱ ግዙፉ ጎሊያድ ተመልሶ በመካከላችን ተገኘ እንዴ “በማለት ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አያይዘውም “ጎሊያድ ተመልሶ መሆን አለበት የአንድን ሀገር አጠቃላይ ህልውና ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ እያለ በዚህ ጉባኤ ፊት መደንፋቱ” ሲሉ ከታዳሚው በኩል የሞቀ ጭብጨባና ሁካታ ተቀብሏቸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማክሰኞው ንግግራቸው ሰሜን ኮሪያን በአጠቃላይ እደመስሳለሁ ማለታቸው ከእንግሊዛ ጠ/ሚ/ር ተሬሳ ሜይ ጀምሮ በበርካታ መሪዎች የተተቹና የተነቀፉ ሲሆን ዋይት ሃውስና በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ለማለሳለስ እንዲጥሩ እንዳደረጋቸው መረዳት ተችሏል።

“እስቲ የእምቢልታዎን ድምጽ በሰላም፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በአብሮነት ዙሪያ ያድርጉት” ሲሉ ዶናልድ ትራምፕን የጠየቁት ሙጋቤ በማከልም “ተ.መ.ድን ከፓሪሱ ዓየር ንብረት ስምምነት ለማውጣት መጣርዎንም በአስቸካይ ሊያቆሙት ይገባል” በማለትም ተናግረዋል።

ዚምባቡዌን ለ37 ዓመታት በመግዛት ላይ ያሉት የ93 ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ ከምእራባውያን ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ከገቡ ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በላይ ሲሆን ምእራባውያኑ በሀገራቸው ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚያደርጋቸውን እርምጃዎች አምርረው የሚቃወሙ ሲሆን ዚምባቡዌም በተለያዩ ማእቀቦች እንደትማቅቅ መደረጓ የሚታወቅ ነው።