ከኦሮሚያ ጉጂ ዞን ቤት ንብረታቸዉ ተቃጥሎ በሚሊሻ ታጣቂዎች እና በቀበሌ አስተዳደሮች አማካኝነት የተፈናቀሉትን የሲዳማን እና የኮሬን ተወላጆችን አገዛዙ በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ወደተፈናቀሉበት ስፍራ እንዲመለሱ እያግባባቸዉ መሆኑ ታወቀ

0

ከሀምሌ ወር ጀምሮ በተለይ በአገዛዙ ልዩ ኃይሎች እና የሚሊኒሻ ታጣቂዎች ተቀነባብሮ በአዋሳኝ ክልሎች መሀከል ሲፈጠር የነበረዉ ፣ግድያ እና ድብደባ የታከለበት  ዜጎችን የማፈናቀል  ሂደት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ካፈናቀለ እና በመቶዎች የሚቆጠሩን ለህልፈተ ሕይወት ከዳረገ በኋላ በተወሰኑ አካባቢዎች አገዛዙ በአሰማራቸዉ የሀገር  ሽማግሌዎች እና የክልል አስተዳዳሪዎች አማካኝነት ወደተፈናቀሉበት ቦታ እንዲመለሱ እያግባቡዋቸዉ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ለዝግጅት ክፍላችን ገለጹ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከጋሞ ዞን ተፈናቅለዉ በእግራቸዉ በመጓዝ ከቀናት በኋላ በደቡብ ክልል ጭሬ ወረዳ ገብተዉ የነበሩት እና ወደ ስምንት ሺ አካባቢ የሚጠጉት የሲዳማ ተወላጆች ትላንት መስከረም 11 ቀን ከጉጂ እና ከሲዳማ ዞን የተዉጣጡ ሽማግሌዎች በጠሩት ስብሰባ ላይ፣”ተፈጥሮ የነበረዉን ግጭት መንግስት ስለተቆጣጠረዉ ተመልሳችሁ ወደነበራችሁበት ለመመለስ ፈቃደኛ ከሆናችሁ የክልሉ አስተዳደር መጓጓዣን እንደሚመድብላቸዉ በመግለጽ ለማግባባት ሞክረዋል።ተፈናቃዮቹም ብንመለስ ተመሳሳይ ችግር ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና አለን?ቤት ንብረቶቻችን ተቃጥሏል፤ ከብቶቻችንም ሞተዋል በማለት ሀሳባቸዉን መግለፃቸዉ የታወቀ ሲሆን፣ ሽማግሌዎቹም የክልሉ መንግስት ከለላ እንደሚያደርግላቸዉ እና ለጠፋዉ ንብረታቸዉ ካሳ እንደሚከፈላቸዉ እንዲሁም ጉዳት ያደረሱባቸዉ ግለሰቦችም ለፍርድ ይቀርባሉ በማለት ከላይ የተሰጣቸውን የማግባባት ስራ መስራታቸው ታዉቋል።

 ከተፈናቃዮቹ መሀከልም አብዛኛዎቹ የሽማግሌዎቹን ንግግር አምነዉ ያልተቀበሉ ሲሆን አንዳንዶች ወደ ደቡብ ክልል ጭሬ ወረዳ  ተፈናቅለዉ ከገቡበት ግዜ ጀምሮ ያሳለፉትን የምግብ እና የዉሀ እጦት እንዲሁም የመኝታን ችግር በማማረር እዛዉ ተመልሰን ሄደን ብንሞት ይሻለናል ሲሉ መደመጣቸዉም ተነግሯል።

 እንዲሁም  ከጉጂ ዞን ተፈናቅለዉ ለአመታት የኖሩበትን አካባቢ ለቀዉ ህወታቸዉን ለማቆየት በተራሮች ላይ ሰፍረዉ የሚገኙትን  የኮሬ ተወላጆችንም የሀገር ሽማግሌዎች እየዞሩ እናንተ ለመመለስ ፈቃደኛ ከሆናችሁ መንግስት እንደ አዲስ  ያደራጃችኋል እያሉ እንደነበር እና ህዝቡ ግን በጥርጣሬ እያያቸዉ እንደሆነ ከተፈናቃዩቹ መሀከል  ያነጋገርናቸዉ  ግለሰቦች  ገልፀዋል።    

 በጎባ ዉስጥ በሚገኙ እና የኦሮሞ እና የሲዳማ ተወላጆች  ተደባለቀዉ  ይኖሩ ከነበሩበት አምስት ቀበሌዎች መሀከል፣ የሁለት ቀበሌዎች ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ባስተዳደር ሀላፊዎች መሪነት እየተደበደቡ፣ ቤቶቻቸዉ እየተቃጠሉ እና ንብረቶቻቸዉን እየተቀሙ  ከሶስት ሳምንታት በፊት ወደ ደቡብ ክልል ቢገቡም፣ የሲዳማ ክልል አስተዳደር በቂ እርዳታ እያደረገላቸዉ እንዳልሆነ፣ ከቀይ መስቀል እና ከመሰል የርዳታ ድርጅቶች የሚመጡ ምግብ እና ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ለተጎጂዎቹ እየደረሱ አለመሆኑን የዉስጥ ምንጮች ተናግረዋል። በእርዳታ ከተሰጡ ቁሳቁሶች መሀከልም እስከ አሁን ለተጎጂዎቹ የሚተኙበት ፍራሽ እንዳልተሰጣቸዉ በመጥቀስ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የሚተኙት መሬት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

 በአዋሳኝ ክልሎች እና ቀበሌዎች ዉስጥ በድንበር ማካለል እና ይገባኛል ሰበብ የተፈናቀሉ ወገኖችን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ እና በፖለቲካው እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ በርካታ ግለሰቦች  የህዉሀት አገዛዝ  እራሱ የፈጠረዉን መፈናቀል እና ግጭት ተቆጣጥሬዋለሁ፣ወደነበራችሁበት ተመለሱ እያለ በህዝብ ስቃይ እና ሞት እድሜዉን ለማርዘም የሚጠቀምበት አካሄድ መሆኑን መረዳት  ያስፈልጋል ሲሉ አስተያታቸዉን ሰጥተዋል።