ራሺያ አንድ ሌ/ጄ በሶሪያ ጦርነት ተሰዋብኝ አለች

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በሶሪያ ዴር ኢዝ ዞር ጦርነት አንድ ከፍተኛ የራሺያ ጄኔራል ከአይ.ኤስ [IS] በተተኮሰ ሮኬት ጥቃት መገደሉን የዛሬይቱ ራሺያ [RT] ዜና ጣቢያ የሀገሪቱን መከላከያ ምኒስቴርን መግለጫ ምንጭ ጠቅሶ ዘገበ።

ላለፉት ሶስት ዓመታት በአሸባሪው አይ ሲ ወይም አይ ኤስ አይ ኤስ [ISIS] ሃይሎች ከበባ ስር የቆየችው ዴር ኢዝ ዞር [Deir ez-Zor] የምስራቅ ሶሪያ ግዛት በራሺያ እና አሳድ ሃይሎች የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ከበባውን ሰብረው አብዛኛውን የከተማ ክፍል መቆጣጠራቸው የተገለጸ ሲሆን የራሺያ ዓየር ሃይልና በሜዴትራኒያን ባህር ካለው የራሺያ ባህር ሃይል መርከቦች ላይ በሚተኮስ ምሽግ ሰባሪ ባልስቲክ ሚሳይል ለሶስት ዓመታት ተከባ የነበረችውን ከተማ ነጻ ማውጣታቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከተማዋ ከአሸባሪው ሃይል ከበባ ነጻ ብትወጣም አሸባሪው ሃይል ላለፉት ሁለት ቀናት የተነጠቀውን ወሳኝ ገዢ መሬት መልሶ ለመያዝ የከፈተውን የአጸፋ ማጥቃት ለመመከት የራሺያው ጄኔራል በከተማዋ እንደተገኙ ዘገባው ገልጾ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከአሸባሪው በተከታታይ በተተኮሰ የሮኬት ጥቃት ሌ/ጄ/ል ቫለሪ አሳፖቮ [Lieutenant-General Valery Asapov] መገደላቸውን ዘግቧል።

የደማስቆ በሽር አል-አሳድ መንግስት ከራሺያ ወታደራዊ ሃይል፣ ከኢራን እና ሒዝቦላህ ሃይሎች ጋር በመተባበር ባለፈው ዓመት መስከረም 2016 ጀምሮ በአሸባሪው ሃይል ላይ በከፈተው ሶሪያን ነጻ የማውጣት ወታደራዊ ዘመቻ 85% በአሸባሪው ቁጥጥር ስር የነበሩትን ግዛቶች ማስመለስ መቻሉ ተገለጸ። በዚህ ዘመቻ በአጠቃላይ 37 የራሺያ ጦር ሃይል ባልደረቦች መገደላቸውን ሞስኮ ይፋ አድርጋለች።

የሌ/ጄ/ል ቫለሪ አሳፖቮ ለሀገሩና ለሶሪያ ህዝብ ሲል ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለከፈለው መስዋእትነት የሞስኮ መንግስት የብሔራዊ ጅግና አቀባበር እንደሚያደርግለት ከመከላከያ ምኒስቴር መግለጫ መረዳት የተቻለ ሲሆን ጄኔራሉ በሶሪያ ካሉት የራሺያ ጦር ሃይሎች ውስጥ ከፍተኛው የጦር መኮንን ነው ተብሏል።