በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች የፌደራል ፖሊሶች እየሰፈሩ መሆናቸዉ ታወቀ፤ ሁኔታዉ ከኢሬቻ በአል አከባበር ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ገልፀዋል

0

ከመስከረም 28 ቀን  ጀምሮ  በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የፌደራል  እና ቀይ ለባሽ ፖሊሶች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች መስፈር መጀመራቸዉን የደረሰን ጥቆማ ሲያመለክት የፊታችን እሁድ መስከረም 21 ቀን በሚከበረዉ የኢሬቻ በአል ላይ የመንግስት አካለትም ሆኑ መሳሪያ የያዙ አካላት  በአሉ ወደሚከበርበት ስፍራ እንዳይገቡ የተደረገዉ ስምምነት አገዛዙን ስጋት ዉስጥ ስለከተተዉ እየተደረገ ያለ ከበባ ነዉ ሲሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል። እንዲሁም  ያአይን እማኞች እንደተናገሩት ዓርብ ከማለዳ ጀምሮ በሱሉልታ የቻይና ቆዳ ፋብሪካ በነበረዉ እና ባካባቢዉ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት በማድረሱ በህዝብ አቤቱታ በተዘጋዉ በወ/ሮ አዜብ መስፍን ፋብሪካ ጊቢ ዉስጥ ሶስት ገልባጭ መኪና የፌደራል ፖሊሶች መራገፋቸዉን ለዝግጅት ክፍላችን አስታዉቀዋል።

ባለፈዉ አመት ባገዛዙ ታጣቂዎች ምክንያት የተከሰተዉን የዜጎች እልቂት በማንሳት ያባገዳ አባቶች ከአገዛዙ ጋር አድርገዉታል የተባለዉ እና የመንግስት አካላትን ሙሉ በሙሉ ያገለለዉ ስምምነት የህዋት አገዛዝን ከፍተኛ ዉጥረት ዉስጥ ከቶት እንደሚገኝ ከተለዩ ቦታዎች የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ሲሆን ከዉስጥ ምንጮች ለማረገጋጥ አንደተቻለዉ ከእለተ ሰኞ መስከረም 15  ቀን ጀምሮ የመከላከያ  እና የፌደራል ፖሊስ አዛዦችን  ያካተተ ዝግ ስብሰባ ሲካሄዱ እንደከረመ ታዉቋል፡፡ በስብሰባዉም ላይ አንዳንዶች መንግስት  ያደረገዉ ስምምነት የበለጠ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ጠቅሰዉ ውሳኔዉ እንደገና እንዲታይ መጠየቃቸዉም ታዉቋል። በስብሰባዎቹ ላይ ከነበሩ አካላት ለመረዳት እንደተቻለዉ አገዛዙ ወደ በአሉ ቦታ ምንም አይነት የፖሊስ እና የመከላከያ  አባላት አላስገባም ይበል እንጂ ሲቪል የለበሱ እና በስዉር መሳሪያ  የታጠቁ  ፌደራሎችን እንደሚያስገባ በዉስጥ ስምምነት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

በተዘያያዘ ዜናም የኢሬቻን በአል፣ ህዋት ባሰበዉ መልኩ እንዲከበር  የኦህዴድ አባላት በመላዉ ኦሮሚ  ክልል  የአስፈፃሚነቱን ስልጣን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እና ለዚህም ከየቀበሌዉ ለተዉጣጡ ወጣቶች  ባህላዊ አልባሳትን እና የዉሎ አበልን በማዘጋጀት ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል ሲሉ የዉስጥ ምንጮች ይገልፃሉ። ስልጠናዉም ምን መለበስ እንዳለበት፤ ምን አይነት ባንዲራ መያዝ እንዳለበት፤ ምን አይነት ዘፈኖች መዘፍን እንዳለባቸዉ እና እንዲሁም ወደ በአሉ ቦታ እንዴት መግባት እና መዉጣት እንዳለባቸዉ አመራርን የሚሰጥ፤ በተጨማሪም በዝግጅቱ ላይ የሚፈጠረዉን ሁኔታ እየተከታተሉ ላገዛዙ አካላት መረጃ ማቀበልን የሚያጠቃልል  እንደነበረም ታዉቋል።

በሌላ በኩል በኢሬቻ በአል ላይ ለመታደም ከመላዉ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ህዝብ ሊገኝ እንደሚችል ሲጠቀስ  በኦሮሚያ  ክልል ባሉ ከተሞች ዉስጥ በአሉ ላይ ሁሉም እንዲገኝ በእድር እና በማህበር ሳይቀር ቅስቀሳዎች እየተደረጉ መሆናቸዉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። እንዲሁም  በአሁኑ ወቅት አገገዛዙ እየፈጠረ ያለዉን መከፋፈል እና መለያየት አንዲሁም ግጭት በመቃወም አዲስ አበባን ጨምሮ ከሌሎችም ክልሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን በበአሉ ላይ በመገኘት የሌላዉ ብሄር ተወላጅ ከኦሮሞዉ ጋር ያለዉን አንድነት ለማሳየት መወሰኑ እየተነገረ ይገኟል።