የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሰሜን ኢትዮጲያ ዕዝ ታጋዮች በወያኔ የፀጥታ ኃላፊዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ድርጅቱ አስታወቀ

0

በደቡብ ጎንደር ሊቦ ከምከም ወረዳ ሊቦ ቀበሌ መሽጎ በነበረው የፀረ ሽምቅ አባላት ላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሰሜን ኢትዮጵያ ዕዝ ታጋዮች መስከረም 19  ቀን ድንገተኛ ተኩስ ከፈቱ።

በዚሁ  ከለሊቱ 6:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት ድረስ በቆየው የተኩስ ልውውጥ፤ በዚህ ቦታ የሚገኘውን የወያኔን ፀረ ሽምቅ በዋና አዛዥነት እና በምክትል አዛዥነት ሲመሩት የነበሩ ዋና አዛዥ ማሩ ዋለ እና ምክትሉ ጌትነት ወንዲዬ መሽገውበት እና ማዘዣ ጣቢያ አድርገው ሲጠቀሙባቸዉ የነበሩት ሁለት ሰፋፊ  ክፍሎች ከነ ሙሉ ዕቃቸው መጋየታቸዉን እንዲሁም በቦታው የነበሩት  ሽምቅ ኃይሎች ከነበሩበት ቦታ እንደሸሹ   አርበኞች ግንቦት ሰባት ያደረሰን  መረጃ አመልክቷል። እነዚህ አዛዦች ሆድ አደር በመሆን ለህወሓት አገልጋይ ሆነው የአካባቢውን ህብረተሰብ መኖሪያ ቤት፣ አዝመራ ሲያቃጥሉ እና የህዝቡን የቤት እንሰሳ ሲያርዱ እና ሲዘርፉ የነበሩ መሆናቸዉን ጠቅሶ ይህ ዘመቻ ከአሁን በኋላ ለሆዳቸው በማደር በማንኛውም መልኩ ለህወሓት አገልጋይ በመሆን እየሰሩ በሚገኙ ሁሉ ላይ የሚቀጥል  እርምጃ እና ጥቃት መሆኑም ተገልጿል።

ጥቃቱን ተከትሎም ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ ትላንት ከምሽቱ ከሶስት ሰአት ተኩል ጀምሮ እስከ ንጋቱ 11 ሰአት ድረስ  ሁለት ተዋጊ ሄሊኮፍተሮች ከባህርዳር አየር ኃይል ማዘዣ በመነሳት  ህብረተሰቡ ላይ ስጋትን ለመፍጠር አካባቢዉን ሲዞሩ እንደነበር  የዓይን እማኞች መናገራቸዉንም ጠቅሷል። ስርዓቱ በአሁኑ ሰዓትም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ኃይሎች በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች መግባታቸውን እና ለስርዓቱ አደጋ መሆናቸውን በይፋ ባይገልፀውም በክስ ሂደት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት  ጉዳይ አርበኞች ግንቦት ሰባትን በተደጋጋሚ በመወንጀል እንደሚታወቅም አስታዉሷል።