ፊፋ በ 8 የአፍሪቃ አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ላይ እስከ 30,000 ዶላር የሚደርስ ቅጣት ወሰነ

0

አባይ ሚዲያ ስፖርት ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በ2018 እኤአ ለሚደረገው የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ላይ በቁጥር ስምንት የሚሆኑ የአፍሪቃ አገራት በፈጸሙት ስህተት ምክንያት ለቅጣት መዳረጋቸውን ተዘግቧል።

የናይጄሪያ እግር ኳስ ቡድን ባሳለፍነው ሴፕተምበር 1 ቀን 2017 እኤአ ከካሜሩን አቻው ጋር ባደረገው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚ ላይ የናይጄሪያ ደጋፊዎች ሜዳውን በመውረራቸው ምክንያት ፌፋ ቅጣት ወስኖበታል።

በዚህም ቅጣት የናይጄሪያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን 30,000 ዶላር እንዲከፍል ፊፋ ውሳኔውን አስተላልፏል።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ የ20,000 ዶላር በቅጣት እንዲከፍል በፊፋ ተፈርዶበታል።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ደጋፊዎች አገራቸው ከቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ በሴፕተምበር 5 ቀን 2017 እኤአ ባደረጉት ግጥሚያ ላይ ስፓርታዊ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመዋል።

የማሊ ደጋፊዎች አገራቸው ከሞሮኮ ጋር ለዚሁ የዋንጫ ማጣሪያ በምታደርግበት ግጥሚያ ላሳዩት አግባብ ላልሆነ ስፓርታዊ ተግባር ፊፋ አገራቸውን የ15,000 ዶላር ቅጣት ጥሎባታል።

የሞሮኮ ደጋፊዎች በመልሱ ጨዋታ የማሊ ብሄራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ ባሰሙት ጩሀት ምክንያት ፌዴሬሽኑ 3,000 ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

የዛምቢያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች በአልጄሪያ ተጫዋቾች ላይ የተለያዩ ነገሮች በመወርወራቸው ምክንያት የ7,000 ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተፈርዶበታል።

የጋቦን ብሄራዊ ቡድን መካተት የማይገባውን ጨዋታ ከአይቬሪ ኮስት ጋር ባደረጉት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ ላይ በማሰለፉ ምክንያት ይህንኑ ጨዋታ በፎርፌ እንዲሸነፍ ፊፋ ወስናል።

ይህ ቅጣት ከመወሰኑ በፊት የጋቦንና የአይቬሪኮስት ጨዋታ በአይቬሪ ኮስት 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቅቆ ነበር።

የቡርኪና ፋሶ እና የሴኒጋል የእግር ኳስ ቡድኖችም ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ማድረግ የሚገባቸውን ጨዋታዎች በጊዜ ባለመጀመራቸው ከፊፋ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ተቀብለዋል።