የመኢአድና ሰማያዊ ፓርቲዎች ውህደት ሊፈጽሙ ነው-መሪዎቹ አሜሪካ ገብተዋል

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት [መኢአድ] እና የሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ሆነው ለመታገል ድርጅቶቹ ለመዋሃድ መወሰናቸውን የሁለቱ ድርጅት መሪዎች ከዋሽንግተን ለቪ.ኦ.ኤ ገልጸው በአሜሪካን የሁለት ወር ቆይታቸውም በ3 ዋና ዋና ነጥቦች ዙሪያ ለመንቀሳቀስ እንዳቀዱ ተናግረዋል።

የመኢአዱ መሪ ዶ/ር በዛብህ ደምሴ እና የሰማያዊ ፓርቲ አቻቸው አቶ የሸዋስ አሰፋ ከቪ.ኦ.ኤው ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአሜሪካን የሁለት ወር ቆይታቸው ለማከናወን ያቀዱትን ሶስቱን ዋና ዋና ጉዳይ ሲገለጹ፣ “በሰሜን አሜሪካ የሁለቱን ድርጅቶች የድጋፍ ኮሚቴ ማቋቋምና ማጠናከር፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች መግለጽና ከአሜሪካ ኮንግረስ ጋር በአካል ተቀራርበው ስለ ሀገሪቱና አካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ ሀሳብ ለመለዋወጥ ነው” ብለዋል።
ሁለቱ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ተመዝግበውና ህጋዊ እውቅና አግኝተው ያሉ ድርጅቶች ቢሆንም የህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ በሚወስደው ከፍተኛ የሆነ መብት ረገጣና አፈና ተወካዮቻቸውን ለፓርላማ አባልነት ማስመረጥ ባለመቻላቸው የፓርላማው 538 መቀመጫ በሙሉ በገዢው የኢህአዴግ ፓርቲ አባላት ብቻ በመያዝ ሀገሪቷ በኮሚኒስታዊ አገዛዝ የምትገዛ ሀገር እንደሆነች ይታወቃል።

በተጀመረው የኢትዮጵያውያኑ 2010 ዓ.ም ውስጥ ሁለቱ ፓርቲዎች ተዋህደው ትግሉን በሀገር ቤት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መዘጋጀታቸውን ለጋዜጠኛው ጠቅሰው የውህደቱን አስፈላጊነት በአጽንኦት አስምረውበታል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ከቀናት በፊት በመጪዎቹ ወራቶች ውስጥ በሚካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ላይ እንደ አንድ የተዋሃደ ፓርቲ ለመቅረብና ብሎም ለመወዳደር መወሰናቸውንም ይፋ አድርገው እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ውህደቱ ስርዓቱ ለሚያራምደው የጸረ ተቃዋሚዎች እርምጃ ለመመከት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተካሄደ ነው ሲሉ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የተነጣጥሎ መጓዝ ውጤት ህብረተሰቡን ክፉኛ አስከፍሎታል ተብሎ በተደጋጋሚ ግዜ ተቃዋሚዎች ሲተቹ ይደመጣል። ተቃዋሚዎች በጋራና በህብረት ከመታገል ይልቅ የተናጥል ሩጫ በመያዝ የእርስ በርስ ፉክክር ውስጥ ገቡ እየተባለ ተደጋግሞ የተገለጸ ቢሆንም አልፎ አልፎ ደግሞ ይህንን ትችት በሚያፈርስ ሁኔታ በሀገር ቤት በ1997 እንደ ቅንጅት አይነት ከዚያም በኋላ በዲያስፖራው እንደ አግ7 ዓይነቶቹ የተሻለ ጥምረትና የተቃዋሚዎች ህብረት አቃቁመው መገኘታቸው ይታወቃል።

የዘንድሮው የመኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ የውህደት ውሳኔም በሀገር ቤት ያለውን ሰላማዊ ትግል ጠንከር ባለ አቅምና አደረጃጀት ለመታገል ከመፈለግ የተነሳ የደረሱበት ውሳኔ እንደሆነ ከድርጅቶቹ በርካታ መግለጫዎችና ገለጻዎች መረዳት ተችሏል። የሁለቱ ድርጅቶች ውህደት ያሰቡትን ሰላማዊ ትግል በአግባቡ ማድረግ መቻል አለመቻላቸው በቀጣዮቹ ወራት ማየት የሚቻል ቢሆንም የህወሃት መራሹ መንግስት በሀገሪቷ ውስጥ በአቻነት ተነስተው የሚፈትኑትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠልፎ በመጣልና በማፈን አባዜው በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መድረክ እጅግ እንዲጠብና ብሎም ከእነአካቴው እንዲዘጋ መደረጉ የሚታወቅ ሃቅ ነው።

አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ መሪ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለውን የሁለቱን ክልሎች ጦርነት የህወሃት መራሹ ጎሳን እና ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፖሊሲ ብሶት መገለጫ ድርጊት ነው ሲሉም ገልጸውታል።