እስራኤል ከኩርድ ኢራንና ቱርክ ከኢራቅ ወግነው ተፋጠዋል

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ባለፈው መስከረም 25ቀን ሕዝበ ውሳኔ ባደረጉት የኢራቅ ኩርድ ህዝቦች ከኢራቅ የመገንጠል ውሳኔን ለመወጋትና ብሎም የኢራቅን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት ለመከላከል አንካራና ቴህራን በጋራ ሊዋጉ መስማማታቸውን የዜሬዪቱ ራሺያ [RT]ዜና ጣቢያ ዘገበ።
በቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዳጎን እና በኢራኑ አቻቸው ሀሰን ሮሃኒ መካከል በቴህራን በተካሄደው ስምምነት መሪዎቹ “ሁለተኛዋ እስራኤል”ያላትን የኢራቃን ኩርዲስታን ራስ ገዝን የነጻነት ህዝበ ውሳኔ አብረው በጋራ በመዋጋት ውጥኑን እንደሚያከሽፉ የዛቱ ሲሆን የኩርዶቹንም ተግባር የሞሳድ በማለት በመካከላቸው ሊፈጠር እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

በኢራቅ የኩርድ ሕዝብ መስከረም 25ቀን ባደረገው ሕዝበ ውሳኔ ከኢራቅ ተነጥሎ የራሱን የኩርዲስታን ሪፐብሊክን ለማወጅ ከ92% በላይ ያለው ህዝብ ድምጽ መስጠቱን ተክትሎ እንዲሁም በሶሪያ እየተካሄደ ባለው የአሳድ መንግስት መራሹ ሃይል በድል ላይ ድል እየተጎናጸፈ መምጣትን ተከትሎ መካከለኛው ምስራቅ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍና ብሎም አዲስ የበላይነት ፍልሚያዎች ከወዲሁ ሲያቆጠቆጡ ይታያል።

በዚህ ዙሪያ የተጠናቀረው ልዩ ዘገባ እንደሚከተለው ቀርባል።
**በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠሩ አዳዲስ የሃይል አሰላለፎችና ህዝባዊ ሃይሎች-

የመከካለኛው ምስራቅ ቀጠና በ2011 የፈነዳው የዓረብ አብዮትና በኢራቅ ደግሞ ቀደም ብሎ በ2003 የገባው ወራሪው የአሜሪካ ሰራዊት ለክልሉ አዳዲስ ሀገራዊ፣ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ሃይሎችን ፈጥራል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዳጎን እና በኢራኑ አቻቸው ሮሃኒ መካከል አንድ ጸረ ኩርድ ግንባር ለመፍጠር መስማማት የዚሁ የለውጡ ማእበል ውጤት እንደሆነ ቢታወቅም መሪዎቹ ግን በመካከላቸው የሞሳድ እጅ እና ተክለቁመና በኩርዲስታን ሕዝቦች ተመስሎ እንዲከስትባቸው ባለመፍቀድ እንደሆነ ተገልጻል።
እንደ ሚታወቀው የኩርድ ህዝብ በኢራቅ፣በኢራን፣በቱርክና በሶሪያ የሚኖር ህዝብ ሲሆን ኢራቅ ቱርክና ኢራን እንደቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመሆን ከፍተኛውን የኩርድ ህዝብ የሚኖሩባቸው ሀገሮች ናቸው።

የየካቲቱ 2003 የአሜሪካ ኢራቅን መውረር በጸጋና በበረከት ከተመለከቱት ኢራቃዊያን ውስጥ የኩርድ ህዝብ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዝ ለጥቆም የሺያ እምነት ተከታዮች ሆነው እናገኛለን።

ኩርዶች በወራሪው የአሜሪካን መንግስት ወታደሮች ያልተቆጠበ ድጋፍና እርዳታ ተደራጁ፣ወታደራዊ አቅማቸውንም እጅግ ያጎለበቱ ሲሆን ድጋፉን ያገኙት እንዲሁ በነጻ ሳይሆን መጀመሪያ የሳዳምን ባዝ ፓርቲ ተዋጊዎች በመዋጋት ለጥቆም ዓለም አቀፉን አሸባሪ አል-ቃኢዳን በመዋጋትና መጨረሻም አሁን ዋነኛውን አሸባሪና እራሱን የእስላማዊ መንግስት ነኝ ብሎ የሚጠራውን አስፈሪ ሃይልን ከኢራቅ ብሄራዊ ጦር በበለጠ ሁኔታ በመዋጋት የጎረፈላቸውን ድጋፍ እንዳገኙ መረዳት ይቻላል።

ፈተናውና የአሜሪካንና እስራኤል ድጋፍ የኩርዶቹን ወታደራዊ አቅም ያፈረጠመ ሲሆን በአንጻሩም የባግዳዱ ማእከላዊ መንግስት ወታዳራዊ አቅምና ጥንካሬ ደካማነት ኩርዶቹን የመስከረም 25ቱን ህዝበ ውሳኔን ያለ ባግዳድ እውቅና እና ድጋፍ እንዲያካሄዱ ድፍረት ሆናቸዋል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።
ኩርዶች ዛሬ ጠንክረዋል። ወታደራዊ ሃይላቸውና የውጊያ ችሎታቸው ተፈትኖ ታይታል።በታሪካቸው ያላገኙትን ታላቅ የራስ ገዝ [Kurdistan Regional Government]የሚባል መስርተዋል። ሆኖም በቃኝ አላሉምና ለሙሉ ነጻነት እውጃ ህዝበ ውሳኔ ሄደዋል።
የተማመናት አሜሪካ አላውቃችሁም ብትላቸውም እስራኤል ግን ከጎናቸው በመቆምና ለውሳኔያቸውም እውቅና በመስጠት ከዓለም ብቸኛዋ ሀገር ሆናለች።

የኩርዶቹ ከእስራኤል ጋር መወዳጀት ባግዳድን ብቻ ሳይሆን ተጎራባች ሀገራትን ቴህራንን፣አንካራን፣ደማስን እና የሂዝቦላውን ሀሰን ነስሩላህን ክፉኛ አስቆጥታል-ብሎም ውጥኑን በእንጭጩ ለመቅጨት ሁሉንም አስማምቶ የጋራ ግንባር እንዲፈጥሩ አድርጋል።
በሌላ ግንባር በኩል የኢራን ክልላዊ ተጽእኖ እጅግ እየጨመረ መሄድ ያሰጋቸው ሁለት የእርሰበርስ ባላንጣዎች እስራኤልና ሳኡዲ ዓረቢያ በሶሪያ የበሽር አል-አሳድና አጋሮቹ ራሺያ፣ኢራን እና ሒዝቦላህ በድል ላይ ድል እየተጎናጸፈ መምጣት ክፉኛ አስግታቸው የውስጥ ለውስጥ ስምምነት እና ትብብር እንዲያደርጉ ሲያስገድዳቸው ይታያል።
በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲዎች ስጋት ለንጉሳዊው የሳኡዲ መንግስት ብቻ ሳይሆን ለአይሁዳዊው የእስራኤል መንግስት በመሆኑ በይፋም ባይሆን በምስጢር ሁለቱ ተጻራሪ ሃይሎች [የእስራኤልና የሳኡዲ ዓረቢያ ማለት ነው] እርስበርስ መረዳዳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

በእስራኤል በኩል በኢራቅና በሶሪያ ያለውን የእስላማዊ መንግስት መደምሰስ ማግስት የሚተካው ሃይል ጸረ ቴላቪቭ የሆኑ ሃይሎች ይሆናሉ የሚለው ሁኔታ እጅግ ያሰጋታል። እናም በአሸባሪው እስላማዊ መንግስት መደምሰስ በሃላ የእስራኤል ጸሮች ከመጠናከራቸው በፊት የሚያግድ ሃይል ያስፈልጋል በማለት የኢራቁ ኩርድ ህዝብ ለመሳሪያነት ታጭተዋል ሲሉ ከሀሰን ነስሩላህ ጀምሮ የኢራን፣የቱርክ፣የሶሪያና የኢራቅ መሪዎች በአንድ ድምጽ ይናገራሉ።
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዳጎን “The independence referendum in the Iraqi Kurdistan is a “betrayal” of the Middle East and a threat to the future of the entire region, በኢራቅ ኩርዲስታኖች የተካሂደው ህዝበ ውሳኔ በኢራቅ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ መካከለኛው ምስራቅ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደትና ለክልሉም የወደፊት ህልውና ከፍተኛ አደጋ የሆነ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

በቱርኩ ፕሬዚዳንት የቴህራን ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒ እና ከሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ኮምኒ ጋር የተወያዩ ሲሆን ኮምኒIsrael as well as some “foreign powers,” including the US, want to create contention between regional powers in the Middle East by creating a “new Israel.”

እንደ እስራኤል እና አሜሪካ ያሉ ሃይሎች በመካከላችን አወዛጋቢና የምታጋጭ የሆነች አዲስ እስራኤል መሳይ በመሀላችን ለመፍጠር ያደረጉት ውሳኔ ነው ሲሉ የኩርዲስታኑን ህዝበ ውሳኔ ምንነት ተናግረዋል።
የኢራቅ ፓርላማ ለጠ/ሚ አባዲ ወደ ኩርዲስታን ግዛት ጦር እንዲያዘምት የሚፈቅድ ህግ አስተላልፎ ጠ/ሚ/ሩ ማንኛውንም ሃይል በመጠቀም የኢራቅን ሉዓላዊነት እንዲያስጠብቅ ውሳኔ አስተላልፋል።

ቱርክና ኢራን ከወዲሁ ሰራዊታቸውን ያሰማሩ ሲሆን የኢኮኖሚም ማእቀብ ጥለዋል።

የኩርዲስታኑ መሪ መሀመድ ባርዛኒ ከህዝበ ውሳኔው በሃላ ይህን ያህል የጠነከረ ክልላዊ ተቃውሞና በተለይም ከዋና ሸሪካቸው አሜሪካን እውቅና እነፈጋለሁ ብለው እንዳልገመቱና እንዳልጠበቁም ይነገራል። ሆኖም ኤርዳጎን “እስራኤል አታድናችሁም ” እንዳላቸው እስካሁን ለህዝበ ውሳኔው ድጋፍና እውቅና የሰጠችው እስራኤል ብቻ ስትሆን እንዴት እንደምትረዳቸው ወደፊት የምናየው ይሆናል።