በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሥራና የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መቋረጡ ተነገረ

0

በምሥራቅ ኢትዮጵያ ባሉት ከተሞችና ገጠር ቀበሌዎች ያለው የሥራና የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መቆሙ ተነገረ።

የኦሮሚያ ቄሮዎች እያካሄዱ ባሉት ሕዝባዊ አመፅ የጫት የቡና የድንች የሽንኩርት የቲማቲምና የመሳሰሉት ትራንስፓርቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጡ አድርገዋል ተብሏል።

የአመፁ መነሻ የሶማሌ ላንድ መንግስትና የሱማሌ ክልል መንግስታት የአወዳይን ጫት አንቀበልም በማለታቸውና ብዙ የአወዳይ ጫትም በመከላከያ ሠራዊት በሚደገፈው የሱማሌ ክልል ሚሊሻዎች እንዲዘረፍና እንዲበላሽ በመደረጉ ነው ተብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጫትና የመሳሰሉትን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ማንኛቸውም ተሽከርካሪዎች በቄሮዎች እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል። በዚህም መሠረት ከምዕራብ ሐረርጌ እስከ ሱማሌ ክልል ወሰን ድረስ ያለው የአስፋልት መንገድ ግራና ቀኝ ከተሽከርካሪዎች በተሰባበሩ የመስታወቶች ተሞልተዋል ተብሏል።

በድብቅ ተጭኖ የተገኘ ጫትም በየቦታው መዘረፉም ተነግሯል። ገበሬዎችም ከቄሮዎች ጋር በመተባበር ሌሊት ሌሊት በአስፋልት ዳር በማድፈጥ የወያኔን መከላከያ ሠራዊትና የፓሊስ ኃይል በወንጭፍ በማጣደፍ መፈናፈኛ አሳጥተዋቸው እንደሚያድሩ የሠራዊቱ አባላት ለሕብረተሰቡ ሲናገሩና ሕብረተሰቡም ሲገልፅ ይሰማል።

ይህ ጥቃት አየተፈፀመ ያለው የፌዴራል መንግስቱ እቆጣጠረዋለሁ በሚለው ከአዲስ አበባ ጂጂጋ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲሆን ምንም እንኳን የፌደራል ፓሊስና የመከላከያ ሠራዊት በመንገዱ ፈሰው ቢታዩም አመፁን መቆጣጠር እንደተሳናቸው በየመንገዱ ላይ በቄሮዎች በተወሰደው እርምጃ የረገፉት የተሽከርካሪ መስታወቶች በቂ ማስረጃ ናቸው።

ይሄንኑ ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ጭር ብለዋል። በሐረር ከተማ የሽንኩርት የቲማቲምና የድንች እጥረት መከሰቱም እየተነገረ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጫት ከአዲስ አበባ ለሱማሌ ክልልና ለሶማሌ ላንድ በአውሮፕላን እየተላከ ነው የሚል መረጃ ለቄሮዎች ስለደረሳቸው ጫት ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ጥሪ አድርገው ወደ አዲስ አበባና አካባቢዋ ጫት በሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

በእነዚሁ አካባቢዎች ሰሞኑን በተካሄዱት ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች በዙ ዜጎች መጎዳታቸውም ተገልጿል። ከትናንት በስቲያ በዓለማያ ከተማ በተደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ አንድ ሰው በመከላከያ ሠራዊት በጥይት መቁሰሉም ይታወሳል።

oromos-displaced