የኒውክሌር መሳሪያዎችን ለማጥፋት የሚታገለው ድርጅት የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የዘንድሮ የኖቤል ሰላም ሽልማትን የኒውክሌር መሳሪያዎችን ለማጥፋት ዓለም አቀፍ ዘመቻ እያደረገ ያለው ይቻላል [Ican] ድርጅት አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ።

ዓለም በአሜሪካን እና ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦርነት ስጋት ደመና ባንዣበበባት በአሁን ሰዓት የኖቤል ሽልማት ሰጪው ኖርዌጂያዊያኑ ድርጅት በጸረ ኒውክሌር መሳሪያዎች ላይ ዘመቻ እያደረገ ያለውን ዓለም አቀፍ ተቋም መሸለም መቻሉ ብዙዎችን በተለይም ሰላም ወዳድ የሆኑትን እንዳስደሰተ ከተሰራጩት ዘገባዎች መረዳት ተችሏል።

በእንግሊዝ ሀገር የሚታተመው ዘጋርዲያን የኖቤል ሽልማቱ የተሰጠው የይቻላል [Ican] ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መጀመሪያ የቴሌቪዥን ቀልድ [Ican director thought the prize was ‘a prank’] ነበር የመሰለው በሚለው አርእስት ስር የ92 ዓመቱን እና የሂሮሺማ ኒውክሌር ቦምብ ተራፊ የሆነችውን ጃፓናዊቷን ሱናኦ ቱሱቦይን በማነጋገር በዘገባው በህይወት ኖረው ይህን በማየታቸው እጅግ መደሰታቸውን ገልጾ “በህይወት እስካለሁ ድረስ ከICAN እና ሌሎች ድርጅቶችና ሰዎች ጋር ሆኜ ከኒውክሌር መሳሪያ የጸዳች ዓለም ለመፍጠር እጥራለሁ” ሲሉ እድሜ ጠገቡን የኔውክሌር ቦምብ ጥቃት ተራፊ የሆኑትን ጃፓናዊ ቃል አስፍሯል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ አሜሪካ በጃፓን ሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ በጣለችው ሁለት የኒውክሌር ቦምቦች ጥቃት በሂሮሺማ ከ80 ሺህ በላይ በናጋሳኪ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን እስከአሁን ድረስ ግን በኒውክሌር የጦር መሳሪያ በታጠቁ ሁለት ሀገራት መካከል የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ በማዋል የተዋጉ ሀገሮች እንደሌሉ ይታወቃል።

የICAN ዓለም አቀፍ ድርጅት አባላቱ ወጣቶች የሚበዙበትና ከመቶ በላይ ሀገራትን በአባልነት ያቀፈ የጸረ ኒውክሌር መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሆን 5ቱ ባለ ኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት የሆኑት ሃያላን ሀገራት አሜሪካ፣ ራሺያ፣ ቻይና፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ የሌሉበት ተቋም እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

ከ5ቱ ባለ ኒውክሌር ሃያላን ሀገራት ሌላ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ እስራኤልና ሰሜን ኮሪያም የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት በመሆን የታወቁ ሀገሮች ሲሆኑ በኢራን በኩል ግን ገና በሂደት ላይ እንዳለች ለማቆም ተስማምታ መፈራረሟ ይታወቃል።

በዘመናችን በሁለት የኒውክሌር ጦር መሳሪያን በታጠቁ ሀገራት አሜሪካን እና ሰሜን ኮሪያ መካከል የኒውክሌር ውጊያ አይቀሬ ነው የሚያስብሉ ተግባራት ከዋሽንግተን እና ከፒዮንግያንግ በኩል በየእለቱ እየተፈጸመ ባለበት ሁኔታና ዓለም አቀፉም ማህበረሰብ በዚሁ ስጋት ውስጥ በተወጠረበት ሰዓት የኦስሎው የኖቤል ሽልማት የጸረ ኒውክሌር መሳሪያ ተቋም [ICAN] በመምረጥ የ1.1 ሚሊዮን ዶላሩን የገንዘብ ሽልማት ሊሸልም በመብቃቱ ዓለም የአሜሪካንን እና ሰሜን ኮሪያን እሰጥ አገባ በአድናቆት አለማየቱን ገላጭ ነው ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል።

አሸናፊው ተቋም [ICAN] ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንድ ጄኒቫ ካ. በማድረግ ከሌሎች የጸረ ኒውክሌር መሳሪያ ድርጅቶችና መንግስታዊ አካላት ጋር በመተባበር የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እገዳን የተመለከተው ውል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት እያደረገ ያለ ተቋም ሲሆን እስካሁን ድረስ ያጸደቁት ሀገራት ቁጥር ግን ሶስት ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። እንዲጸድቅ የተፈለገው ውል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ122 አባላት ሀገራት ፊርማ ባለፈው ሐምሌ ተቀባይነት ቢያገኝም ዓለም አቀፋዊ ስምምነት እንዲሆን ግን ቢያንስ በ50 ሀገራት መጽደቅ እንዳለበት የተ.መ.ድ መተዳደሪያ ቻርተር ይደነግጋል።

የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሽልማታቸውን የሚረከቡት በመጪው ህዳር [2017] ወር መገባደጃ ላይ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሚደረግ ስነ ስርዓት እንደሆነ መረዳት ተችሏል።