ስራ የሚለቁ ፖሊሶች ቁጥር ከተገመተው በላይ በመሆኑ የፖሊስ ኮሚሽን መስሪያ ቤት እስከ ታህሳሥ መልቀቅ እንደማይቻል ማስታወቁ ታወቀ

0

በተለይ ካለፈዉ አመት ተቃውሞ በሗላ በከፍተኛ ቁጥር የሚገመቱ ፖሊሶች መልቀቂያ በማስገባት ስራቸዉን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸዉን ሲገልፁ የፌደራል ፖሊስ መስሪያ  ቤቱ ታዉጆ የነበረዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከመነሳቱ በፊት ስራ መልቀቅም ሆነ የእረፍት ፈቃድ መጠየቅ እንደማይቻል በወሰነዉ ዉሳኔ መሰረት የፖሊስ አባላቱ ካለዉዴታቸዉ በስራዉ ላይ እንዲቆዩ መገደዳቸዉን በማስታወስ፣ ቃል በተገባላቸዉ መሰረት በተጀመረዉ አመት ስራቸዉን ለመልቀቅ ጥያቄ ቢያቀርቡም  በቀላሉ ምላሽ አለማግኘታቸዉን ተናግረዋል። መልቀቂያ ማስገባታቸዉን በመጥቀስ መሸኚያ እንዲሰጣቸዉ በመጠየቅ ላይ የሚገኙ ፖሊሶች፣ ከፌደራል ፅህፈት ቤት በተዉጣጡ አመራሮች ”የተለየ እቅድ ከሌላችሁ በስተቀር ምን ጎሎባችሁ ነዉ እንለቃለን የምትሉት?” በማለት ጥያቄ ያቀረቡላቸዉ መሆኑን ተናግረዉ ፖሊሶቹ ሀሳባቸዉን በመቀየር ለአምስት አመታት ለማገልገል የሚፈርሙ ከሆነ በመረጡት  ዩኒቨርስቲ ዉስጥ ምንም አይነት የመግቢያ  ነጥብ ሳይጠየቁ ሊማሩ የሚያስችላቸዉን  ነፃ የትምህርት እድል ሊያሰጣቸዉ እንደሚችልና የደሞዝ ጉዳይም በሂደት እንደሚታይላቸዉ ተነግሯቸዋል።

ሆኖም ከፖሊሶቹ አባባል ለመረዳት እንደተቻለዉ ምንም አይነት ማባበያ ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸዉ፤ ባለስልጣናቱ እነሱ የሚለቁትን ቦታ ተክተዉ ሊሰሩ የሚችሉ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ አዲስ  ሰልጣኞች ከጦላይ ለማምጣት ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ተናግረዉ አዲሶቹ ፖሊሶች እስኪመጡ ድረስ ቢያንስ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ በስራቸዉ ላይ ለመቆየት እንደሚገደዱ ተነግሯቸዋል።

የፌደራል እና የከተማ ፖሊሶች ከሚሰሩባቸዉ ቦታዎች መሀከል በተለይ በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙ ፖሊሶች ከዘጠና በመቶ  በላይ ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸዉን ከዉስጥ የሚወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ፤ በቃሊቲ አስር ቤት ዉስጥ በሚደረጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በእስረኞች ላይ በሚፈፀሙት ስቃዮች ምክንያት በርካታ ፌደራሎች እና ፖሊሶች ለመስራት የማይመርጡት እና በተደጋጋሚ ዝውውር የሚጠየቁበት ማረሚያ  ቤት በመሆን እንደሚጠቀስም ይነገራል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ባለፈዉ አመት በትንሹ ከአንድ ክፍለ ከተማ  ዉስጥ ከአርባ አምስት በላይ ፖሊሶች መልቀቂያ በማስገባት ስራቸዉን የሚለቁበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ቢገኙም  የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደተነሳም መሸኛቸዉን ለጠየቁ የአዲስ አበባ ፖሊሶች የኢሬቻ በአል ከማለፉ በፊት መልቀቅ አትችሉም የሚል ምላሽ እንደተሸጣቸዉ ተናግረዉ፣ አሁን ደግሞ እስከ ታህሳስ ጠብቁ መባላቸዉ እንዳበሳጫቸዉ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል። ባንዳንድ ፖሊስ መምሪያዎች የተወሰኑ ፖሊሶች በኢሬቻ በአል ላይ በነበረዉ ተቃውሞ ተባባሪ ነበራችሁ፤ አብራችሁም ጨፍራችሗል ተብለዉ ለግምገማ እንደተጠሩም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።