አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ የሆኑት አቶ አባዱላ ገመዳ በገዛ ፍቃዳቸው ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተዘገበ።

አፈጉባኤው የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን ያስገቡት ላገለገሉበት ሕዝብ ተወካዮች ሳይሆን ለመንግስት በመሆኑ በጥያቄያቸው መሰረት ተፋጺሚነት ያገኛል ተብሎ የተገመተ ሲሆን ሁለት እድምታን ይያዛል ተብሎ ይገመታል። አንደኛው አፈ ጉባኤው አባዱላ ገመዳ በኦህዴድ ውስጥ በገነቡት ፈርጠም ያለ ሃይል በመተማመን እና የህወሃትን ሃይል መዳከም በማየት በምስራቅ ኢትዮጵያ ከ100 ሺህ በላይ የኦሮሚያ ተወላጆች ተፈናቃይ የሆኑበትን የሶማሌ ግጭት በውጭ ሆነው ለመምራት ከማሰብ የመነጨ ነው ሲሉ፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ገዢውን የህወሃት ሃይል በስራ መልቀቅ ስም የተበላሸውን የኦህዴድ ስራን እንዲያጸዱለት ለማመቻቸት ነው ተብሎ ተግምቷል። በመንግስት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

በትግራይ እየተካሄደ ያለው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ልዩ የተባለውም ስብሰባ እየተካሄደ ሲሆን ሳምንት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ስልጣናቸውን ለቀው ከከዱት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አባዱላ ገመዳ 3ኛው ባለስልጣን ሲሆኑ ከሁለቱ ቀደምት ባለስልጣናት የሚለዩት አባዱላ ስልጣናቸውን ሀገር ውስጥ እያሉ ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ነው።

የቀድሞው ደርግ ወታደር ምርኮኛ ምናሴ ተክለሃይማኖት በኋላ ላይ አባዱላ ገመዳ የጦር ጄኔራል ተሹመው የነበሩና በህወሃት ክፍፍል ወቅት ከውትድርናው ተነስተው በኦሮሚያ በፕሬዚዳንትነት የተሾሙ ሲሆን ሰውዬው በፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው በአቶ መለስ ባለመወደድ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ ተደርገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተደርገው የተሾሙ ናቸው። አባዱላ ገመዳ ከሚታሙበት የሙስና ዘረፋም ሌላ በኦህዴድ ውስጥ ተጽእኖ አድራጊ ጠንካራ መሰረት ያለው ሃይል እንደመሰረቱ በሰፊው ይነገርላቸዋል።

በመንግስት በኩል በይፋ መልቀቁ ባይታወጅም አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ግን ሙሉ በሙሉ ስራቸውን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል። የአባዱላ ገመዳ ስልጣን መልቀቅና ብሎም ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት በሳምንት ግዜ ውስጥ መክዳት የገዢው ፓርቲን መታደስ በማይችልበት ሁኔታ መበስበሱን ያረጋግጣል ይላሉ ታዛቢዎች።