በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በኦሮምያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮችን ምክንያት በማድረግ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ዳግም ሊያገረሽ እንደሚችል ስጋት እንዳላቸው በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች እየገለፁ ነው

0

በተለይም ማክሰኞ መስከረም 23 ቀን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስትና የሀገር ሽማግሌዎች አወጡት ተብሎ በክልሉ ድረ ገፅ የተሰራጨው ዘገባ ይዘትና  ግጭቱን አስመልክቶ ሌሎች በድረ ገፁ እየተሰራጩ ያሉት መረጃዎች የሁለቱን ክልል ወንድማማች ህዝቦች ለሌላ ዙር ግጭት የሚያነሳሳ እንደሆነ ትንሳኤ ያናገራቸው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ገለፁ። እንደነዋሪዎቹ ገለፃ ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ህዝቦችን በህዝቦች ላይ በማነሳሳት ወደግጭትና እልቂት እንዲያመሩ የሚገፋፉ ዘገባዎችና ንግግሮች ከመንግስት አካላት መደመጥና መዘገብ መቀጠላቸው ለስጋታቸው ምክንያት እንደሆነ ተናግረው የህወሀት አገዛዝ በግጭቱ ሂደት ውስጥ ትልቁን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝና ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ከጀርባ ሆኖ ግጭቱን ለማስቀጠል በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ አክለው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስትና የሀገር ሽማግሌዎች ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 23 በጅግጅጋ ከተማ ካሊ1 አዳራሽ ተሰብስበው  አወጡት በተባለው የአቋም መግለጫ ላይ በሁለቱ ክልሎች መካከል ለተቀሰቀሰው ግጭት በምክንያትነት  በ2008 ዓ ም የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ምክንያት አድርጎ በኦሮምያ ክልል ተነስቶ የነበረው ህዝባዊ አመፅ በፌደራል ስርዓቱ ላይ የተጋረጠ አደጋና የደርግን ስርዓት ለመመለስ ያለመ ነበር የሚል ውንጀላ መሰንዘሩ ህወሃት እና የሱማሌ ክልል ሃላፊዎች በተቀናጀ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው የሚል ነቀፌታ አስከትሎአል። ነቀፌታውን እየሰነዘሩ ያሉ አካላት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ህብረተሰባችን የሚያሰማውን ተቃውሞ የህወሃት አገዛዝ በፈዴራል ሥርዓቱ ላይ የተቃጣ ጥቃት የሚል መጠሪያ በተደጋጋሚ ሲሰጠው መደመጡን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።  ከዚህ በተጨማሪ ልዩ ሚሊሽያ በማዝመት በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ላይ የግዲያና ከኖሩበት ቀዬ የማፈናቀል እርምጃ የወሰደው የሱማሌ ክልል አስተዳደር በኦሮሚያ ላይ የጠብ አጫሪነት ክስ መመስረቱም ብዙ እያነጋገረ መሆኑን የክልሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።  

በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል ሰፍኖ ያለውን ውጥረት በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች በሚሰጡት አስተያየት ሁለቱም ክልሎች እርስ በርስ በመወነጃጀል እያወጡ ባሉት መግለጫዎች  ራሳቸውን እንደሉአላዊ ሀገር አድርገው የመውሰድ አካሄድ ማሳየታቸው ህወሀት መራሹ አገዛዝ ከፋፍሎ ለመግዛት ሲል ለ26 አመታት ሀገሪቷ ላይ የጫነው የቋንቋ ፈደራሊዝም የደረሰበትን ደረጃና በአገራችን ሉአላዊነት ላይ የጋረጠውን አደገኛ ሁኔታ የሚያመላክት ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ አደገኛ አካሄድ በቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለትና እርምት ካልተወሰደ ሀገሪቷ ልትወጣው ወደማትችለው የከፋ ችግር ልታመራ እንደምትችልም እያስጠነቀቁ ነው።  

በተለይም ወንድማማች የሆነውን የአንድ አገር ዜጋ በመከፋፈል የአንዱን መከራና ስቃይ ሌላው እንዳይጋራና እንዳይተዛዘን ብሎም የጠላትነት ግድግዳ በመካከላቸው ለመገንባት እንዲቻል ከእኛ ወገን ይህን ያህል ሰው በዚህ መልኩ ተገደለ ወይም ተፈናቀለ የሚሉ ዘገባዎች በሁለቱም ክልሎች ድረገፆች ላይ ሆን ተብሎ  በተከታታይ እንዲወጡ መደረጋቸው ግጭቱ እንዲባባስና ህዝቡ በበቀል እንዲጨራረስ መንገድ የሚከፍት እንደሆነ የትንሳኤ ዝግጅት ክፍል ያናገራቸው የክልሎቹ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አያት ቅድመ አያቶቻችን በቋንቋ፤ በባህል ወይም በሃይማኖት ልዩነቶች ሳይከፋፈሉ  የአገራችንን ህልውና ከባዕድ ወራሪዎች ጠብቀው ያስረከቡን ተዋደንና ተከባብረን በሠላም እንድንኖር እንጂ እርስ በርስ ተበላልተን እነርሱ በህይወት መስዋዕትነት  ያስረከቡንን የጋራ  ቤታችንን ለማፍረስ አይደለም ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ህወሃት በህዝቦች መካከል ሆን ብሎ የሚቀሰቅሰውን ግጭት ለማክሸፍ እያንዳንዱ ዜጋ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ እና ከማናቸውም አይነት የጎንዮሽ ጠብ እንዲርቅ አደራ ብለዋል።

በአንዳንድ ጊዜያዊ ጥቅም ተታለው ከህወሃት ጎን የወገኑና በሁለቱ ክልሎች ግጭት ተዋናይ የሆኑ የሱማሌ እና የኦሮሞ ተወላጆች ተግባራቸው በገዛ ወገኖቻቸው ላይ የሚያስከትለውን መከራና ስቃይ ተገንዝበው አሁኑኑ ከህዝባችን ጎን እንዲሰለፉና የህወሃትን መሰሪ አላማ እንዲያከሽፉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።