አባ ዱላ ገመዳ ነገ ፓርላማ ይገኛሉ-ኢህአዴግ መልቀቂያው አልደረሰኝም አለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ላለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ፓርላማ አፈጉባኤ የሆኑትና የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡት ብ/ጄ/አባዱላ ገመዳ ነገ በሚከፈተው ፓርላማ ላይ እንደሚገኙ የተሰማ ሲሆን ገዢው የኢህአዴግ ፓርቲ በበኩሉ የአፈጉባኤው የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አልደረሰኝም ሲል ገልጿል።
የአፈጉባኤውን የስራ መልቀቂያ ማስገባት እንደተሰማ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከመንግስትና ከራሳቸው ከጄ/ል አባዱላ ገመዳ አንደበት ማረጋገጫ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ ማወቅ ተችሏል።

ሆኖም የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአቶ ሺፈራው ሽጉጤ በኩል ምንም የደረሰኝ መልቀቂያ ደብዳቤ የለም ሲል ለቪ.ኦ.ኤ ጋዜጠኛ የገለጸ ቢሆንም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን የአፈጉባኤውን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት አረጋግጠው እንደምክንያት ያቀረቡትን ነጥብ ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።

የአፈጉባኤውን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ከመንግስት በኩልና በራሳቸው በጄ/ል አባዱላ ገመዳ አንደበት ሊገለጽ ያልተቻለበት ዋና ምክንያትና በገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ “የደረሰን ደብዳቤ የለም” የተባለበት ዋና ምክንያት ጄ/ል አባዱላ ገመዳ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ከሳምንታት በፊት ቀደም ብለው ለመንግስት ያስገቡ በመሆኑና በወቅቱም ፓርላማው በሁለት ወር እረፍት ላይ ያለ በመሆኑ መንግስት ውሳኔውን የሚሰጠው ፓርላማው ነው በሚል የፓርላማውን መከፈት ለመጠበቅ ሲገደድ የስራ መልቀቂያ ያስገቡትም አፈጉባኤ በጉዳዩ ላይ በይፋ ከመግለጽ እንዲቆጠቡ ተነግሮ በነበረበት ሁኔታ ወሬው ሾልኮ ለመገናኛ ብዙሃን ጆሮ በመድረሱ ጉዳዩ ግራ በሚያጋባ መልኩ ለሕዝብ እንደተገለጸ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

አፈጉባኤው የስራ መልቀቂያውን ለሾማቸው ፓርላማ ማቅረብ ሲገባቸውና ውሳኔም ማግኘት የሚችሉት ከፓርላማው ሆኖ ሳለ እሳቸው ግን ለመንግስት ስራ አስፈጻሚው ክፍል በመስጠታቸው ውሳኔ ሊያገኙ እንዳልቻሉና ነገ በሚከፈተው ፓርላማ ላይ ውሳኔ ያገኛሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጽ/ቤት አቶ ሺፈራው ሽጉጤ የአፈጉባኤው የመልቀቂያ ደብዳቤ አልደረሰንም ማለታቸው የአፈጉባኤውን ለፓርቲው አለማስገባት ከመግለጽ ባሻገር የስራ መልቀቂያው በአጠቃላይ እንዳልገባ አድርጎ የሚገልጽ አይደለም ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ግራም ነፈሰም ቀኝ አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ከሳምንታት በፊት እንዳስገቡ በማያሻማ ሁኔታ የተረጋገጠ ሲሆን ስራቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ የበቁበትን ምክንያት ቀደም ሲል አፈጉባኤው ከመንግስት ጋር ሲጋጩበት ከነበረው የምስራቅ ኦሮሚያ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ከመስጠት በስተቀር በይፋ የተገለጸ ነገር እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ ጥርት ያላለ የስራ መልቀቂያ ሁኔታ ላይ ያሉት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ነገ በሚከፈተው ፓርላማ ላይ ሁኔታቸው አጠቃላይ መልስ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።